Get Mystery Box with random crypto!

በስፋት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡      የግብፅ ሌላኛው ሥልት በሃይማኖቶቻችን መ | The Niles ናይል 🇪🇹

በስፋት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡

     የግብፅ ሌላኛው ሥልት በሃይማኖቶቻችን መካከል ያሉትን የግንኙነት ድሮች ለመበጣጠስና በሃይማኖት ሰበብ አገር እንዲተራመስ ማድረግ ነው፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከመንግሥት ጎን እንዳይሠለፍና ከክርስቲያኑ ኅብረተሰብም ጋር ተባብሮና ተከባብሮ እንዳይኖር የአሏህ ሕዝብ (Hizbu-Allah) እና የሰይጣን ሕዝብ (Hizbu Shaitan) በሚል ፈሊጥ እየከፋፈሉ የሕዝቡን አንድነት ለማናጋት መክረማቸው ብቻ ሳይሆን፣ በቅርቡ በአልሸባብ ዳግም ጥቃትም ሞክረዋል፣ የተሳካ ባይሆንም፡፡

     በዚህ ረገድ በውስጣችን ያሉትን አክራሪ ኃይሎች በገንዘብ በማጠናከርና በማደራጀት ይህንኑ የመከፋፈያ መርዝ እንዲረጩ፣ ሁከትና ሽብር እንዲፈጥሩ፣ ወኔ ሰላቢ የሆኑ ፕሮፓጋንዳዎችን እንዲያሠራጩ፣ ከፍተኛና አሰቃቂ የኃይል ዕርምጃዎችን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየወሰዱ ሕዝቡ እንዲሸማቀቅ ለማድረግ መኳተናቸውን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ እኩይ የሆነ የእሾህን በሾህ ሴራ ሥልታቸው በፊትም የነበረና የቀጠለ ነው፡፡

       የግብፅ ፖለቲከኞች  የሚሉትን ሁሉ ቢሉ፣ የሚጮኹትንም ያህል ቢጮሁ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ማድረግ ያለባቸውን እያደረጉ የግድቡን ሥራ አጠናክረው በመቀጠላቸው የተደረሰበት ደረጃ ላይ መድረስ ተችሏል፡፡ ዋናው ሥራን በአግባቡና በትኩረት መሥራት እንጂ፣ የእነሱ ጩኸትና ማስፈራሪያ እንደማይበግረንና ሥራችንን የሚያስተጓጉል የገንዘብና የፀጥታ ችግር እንደሌለብን በተግባር ማሳየት በመቻላችን እንደ ሕዝብና አገር ልንኮራም ይገባል፡፡

      ለወደፊቱም ቢሆን በግብፅ ፖለቲከኞችና ሐሳዊ መሲህ ምሁራን ወሬ መፈታት የለብንም፡፡ የእነሱ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆንም አይገባም፡፡ ስለኃይል ማመንጫ ግድባችን ትክክለኛውንና ወቅታዊውን መረጃ የምናገኝበት ተቀዳሚ ምንጫችን የእኛው የራሳችን መንግሥትና የግድቡ ሥራ ብሔራዊ አስተባባሪው ተቋም መሆን አለበት፡፡ መንግሥትና በዘርፉ ያሉት አዋቂዎችና ሙያተኞች የሚሉንን መስማት ብቻ ይበቃናል፡፡

      በዚህ ረገድ ከብዙ ሥራዎቻችን በተሻለና ለብሔራዊ አጀንዳ ትኩረት የሚሰጡ የማኅበረሰብ አንቂዎችና በቂ የዕውቀት ባለቤቶች አሉን፡፡ ስለወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በአጠቃላይና ስለዓባይ ወንዝ በተለይ ሊያስረዱን የሚችሉ እንደ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ፣  ያዕቆብ አርሳኖ (ፕሮፌሰር)፣ መህመድ አልአሩሲ፣ ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ ጌታቸው ወልዩና የአሁኑ ዘመን ከሚባሉትም እነ ሰላም ሙሉጌታ፣ ሱሌማን አብደላ፣ ስላአባት ማናዬ፣ ደጀኔ አሰፋ፣ እስሌማን ዓባይ (የዓባይ ልጅ) እና ሌሎችም ምሁራን ስለዓለም አቀፍ የውኃ ሕግጋትና ስለወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ፖለቲካ በበቂ አሳማኝ ሁኔታ ሊነግሩን ይችላሉ፡፡

      ስለሆነም ስለዓባይ ጉዳይ መረጃ ለማግኘት ጆሮዋችንን የግብፅ ፕሮፓጋንዲስቶችና ቅጥረኞች አፍ ሥር መደቀን አያስፈልገንም፡፡ የግድቡን ግንባታ ያለማቋረጥ እያስኬድን ጎን ለጎን ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና የሃይማኖት ልዩነቶቻችን ለግብፅ መሰሪዎች መጠቀሚያ እንዳይሆን መሥራት አለብን፡፡ በዚህ ረገድ የሚነሱ ጉዳዩችን በሙሉ በጥንቃቄ እንመርምር፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠንክረንና እንደ አንድ ሰው ሆነን፣ በአንድ ልብ ሊደቀንብን የሚችለውን ተግዳሮት ለመወጣት እየተዘጋጀን ፍፃሜውን ማሳመር ይጠበቅብናል፡፡

     ለነገሩ እስካሁንም ከተፈጥሮ ሀብታችን ላለመጠቀማችን እንቅፋት የሆነችብን ግብፅ ብቻ አልነበረችም፡፡ ሌሎች ውጫዊ ተፅዕኖ አድራጊዎችና የራሳችንም ውስጣዊ የአቅም ውስንነት ነበረብን፡፡ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን በቅኝ ገዥነት ያስተዳድሩ የነበሩ አገሮች በውኃ ሀብቱ ግብፅ ብቻ ተጠቃሚ እንድትሆን በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸው ስምምነቶች፣ እንዲሁም ከቅኝ አገዛዝ በኋላ የግብፅ መንግሥታት ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ለማልማት የገንዘብ ድጋፍና ዕርዳታ እንዳታገኝ ሲያደርጉ ልክ ነው ብለው ሳያመነቱ የተቀበሏቸው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች በውጫዊ ተፅዕኖነት አድራጊነት ይጠቀሳሉ።

     እ.ኤ.አ. ከ1890 እስከ 1950 ድረስ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ቅኝ ገዥዎች (በዋናነት እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጣሊያን) በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ከስድስት ጊዜ በላይ ስምምነቶች አድርገዋል። ሁሉም ስምምነቶች ኢትዮጵያንና ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሕዝቦችን ያገለሉና በዋናነት ግብፅን በተከታይነት ሱዳንን ተጠቃሚ ያደረጉ በመሆናቸው ይመሳሰላሉ።

     ከሁሉም በላይ ግን እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 ግብፅና ሱዳን የናይል ውኃን ብቸኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን የደነገጉበትን የእርስ በርስ ስምምነት አድርገዋል። እ.ኤ.አ. በ1928 ኢትዮጵያን ወርሮ የነበረው የፋሺሽት ጣሊያን መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ልማት ላለማካሄድ ከእንግሊዝ ቅኝ ገዥዎች ጋር ተፈራርሟል። እነዚህ ድርጊቶች ሁሉ በታሪክ ጥቁር መመዝገብ ያለባቸው ናቸው፡፡

     እ.ኤ.አ. በ1959 ለናይል ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላቸው ሁለት አገሮች፣ 86 በመቶ የናይል ውኃ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የራስጌ ተፋሰስ አገሮች ጭራሽ መኖራቸውን በመዘንጋት ስምምነት አድርገዋል። እስከ ዛሬ በዓባይ ውኃ ላለመልማታችን በሁለተኛነት ምክንያት የሆነው ደግሞ በወንዙ ላይ ልማትን በራስ ሀብት ለማከናወን የሚያስችል አቅም ማጣታችን መሆኑን፣ እንደ ትልቅ መመርያ መውሰድ ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡

     እዚህ ላይ ይህ የዓባይ ትውልድ የሚኮራበት ቁም ነገር ያለውን ሀብት አሟጦ በራስ አቅም ግድቡን ለመገንባት በመነሳቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ገና ከጅምሩ፣ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መርሆችን መሠረት የደረገውን የናይል ሁሉን አቀፍ የስምምነት ማዕቀፍ በማርቀቅና በመጨረሻም አብላጫው የተፋሰሱ ሕዝቦች እንዲቀበሉት በማድረግ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራቱ መደላድሉን ምቹ አድርጎታል። ለኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ የሚሆነው እ.ኤ.አ. በ2015 በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመው «Declaration of Principles» በመባል የሚታወቀው ስምምነት ነው የሚባለውም በዚሁ መነሻ ነበር።

    ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተመሠረተ፣ አሥር ዝርዝር ነጥቦችን የያዘና ሦስቱንም የተፋሰሱ አገሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ታሪካዊና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ብዙ የውጭ ተፅዕኖዎች ተደርገውባታል፡፡ ያንን ሁሉ ጫና በጣጥሳ በአሸናፊነት ወጥታ እነሆ የግድቡ ግንባታ ሦስተኛውን ሙሌት አጠናቆ ኃይል ማመንጨት ደረጃ እንዲደርስ አንዱ እርሾ የተፋሰሱ አገሮች በፈራ ተባም ቢሆን የደረሱበት ስምምነት ነው።

     አንዲት ጠብታ ውኃ ለዓባይ ወንዝ የማታዋጣው ግብፅ በእኛ ሀብት ስትከብር ኖራ፣ ዛሬ በራሳችን ገንዘብ በሠራነው ግድብ ስካታብድ መታየቷ ግን አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሁንም ከተጣባት በሽታ አለመላቀቋን ያሳያል፡፡

ካይሮ በቅርቡ የእኛን ግድብ የውኃ ሙሌት ተከትሎ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ጠርታ በ13 ሚኒስትሮች ላይ የሹም ሽር አድርጋለች፡፡ በፀረ ኢትዮጵያዊነት በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ የሚዲያና የማኅበራዊ ሚዲያ ሥልጠና ከመላው አፍሪካ ለተውጣጡ የሚዲያ ሰዎች በተለያዩ ቋንቋዎች በመስጠት፣ በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ ዘመቻ ለመክፈት እንደ አዲስ እየሠራች መሆኗንም ነው ውስጥ አዋቂ መረጃዎች ያመለከቱት፡፡