በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ትምህርት ይጀምራሉ ሲል ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በ2016 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያዉ ወሰነ-ትምህርት ተማሪዎቻቸውን ለመጥራትና መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸዉን ሙሉ ለሙሉ ለመጀመር አልቻሉም ነበር ብሏል ሚኒስቴሩ። በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር ከክልሉ ኮማንድፖስት፣ የጸጥታ አደረጃጀቶችና የሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ሲያካሂድ መቆየቱ ተገልጿል። " የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ፣ የአስሩ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ጸጥታ አካላት ትናንት ታህሳስ 18/2016 ዓ.ም በጉዳዩ ዙሪያ የመከሩ ሲሆን አሁን በክልሉ አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን መጥራትና ማስተማር እንደሚችሉ ውሳኔ ላይ ተደርሷል። " ሲል ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል። በዚህም መሰረት ከጥር 1/2016 ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን ጠርተው የመማር ማስተማር ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል። በመሆኑም በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲዎቹ የሚያደርጉትን ጥሪ እንዲከታተሉ ጥሪ ቀርቧል። @News_For_Student @News_For_Student 14.4K views14:19