Get Mystery Box with random crypto!

ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ የሚገኘው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያ ቀን ውሎ | ትምህርት ሚኒስተር

ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ የሚገኘው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ተጠናቋል።

ከ560 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ130 ማዕከላት ብሔራዊ ፈተናውን እየወሰዱ ሲሆን በ128ቱ ማዕከላት በሰላም ተሰጥቷል፡፡

ፈተናው እየተሰጠባቸው ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በሁለት የመፈተኛ ማዕከላት ችግር ማጋጠሙ ተገልጿል።

በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ በምስራቅ ጎጃም እናርጅ እናውጋ ወረዳ ተማሪዎች ፈተናው ከመጀመሩ በፊት "አንፈተንም" በማለት ለቀው መውጣቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ረፋዱን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የተማሪዎቹ ምክንያት በአግባቡ ተጣርቶ የሚወሰደው እርምጃ ይገለጻል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ የሚገኝ ድልድይ ተደርምሶ በተማሪዎች ላይ አደጋ ደርሷል።

በአደጋው ጉዳት ያጋጠማቸው ተማሪዎች ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን ተማሪዎቹ ካገገሙ በኋላ ፈተናውን እንዲወስዱ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በድልድዩ መደርመስ አደጋ የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን የሲዳማ ክልል ሠላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ተናግረዋል።

በአደጋው 310 ተማሪዎች ቀላልና 110 ተማሪዎች ላይ መካከለኛና ከባድ ጉዳት ደርሷል። 20 ተማሪዎች የአጥንት ስብራት እንዳጋጠማቸው ኃላፊው አስረድተዋል።

ቢሮው ተማሪዎች ተረጋግተው ወደ ግቢው እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ፈተናውን አስመልክቶ የሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡትን መመሪያ እንዲከታተሉ አሳስቧል።

@NEAEA_nea