Get Mystery Box with random crypto!

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤ ነገር ግን 'ባለራዕይና መስራች ነኝ' ብሎ በራሱ ራዕይ የተጠመደ ሳይሆን | ናዝራዊ Tube

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን "ባለራዕይና መስራች ነኝ" ብሎ በራሱ ራዕይ የተጠመደ ሳይሆን "ከሰማይ ለተቀበልሁት ራዕይ እምቢ አላልሁም" የሚል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን የራሱን ክብርና ምቾት ሳይሆን የላከውን ክብርና መታየት የሚፈልግ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ዘይት የሚቸበችብ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ዘይት የረሰረሰ:

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን "እኔና አንተ ከዚህ በፊት ተገናኝተን እናውቃለን?” ብሎ የሚቀልድ ሳይሆን የእግዚአብሔር ጥበብና ሃይል የሆነውን ክርስቶስን የሚገልጥ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ከእግዚአብሔርና የእግዚአብሔርን ምስክርነት እንጂ የሰው ምስክርነት ያላሰከረው:

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ለመወደድ ብሎ የሚያገለግል ሳይሆን እግዚአብሔርን ከመውደዱ የተነሳ የሚያገለግል:

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ከብር ኋላ የሚሮጥ ሳይሆን ራሱን ከሕዝቡ ጋር ጨምሮ ከክርስቶስ ኋላ የሚሮጥ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ጫማውን የሚያስምና መጽሐፍ ቅዱሱን በአሽከር የሚያሸክም ሳይሆን ራሱን ክዶና መስቀሉን ተሸክሞ ከፊት የሚወጣ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን "ብር ትራሱ" የሆነ ሳይሆን ካለው የሚያካፍልና አገልግሎቱም እንደ ኢየሱስ ድሆች ላይ ያተኮረ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በቲፎዞና በጋሻ ጃግሬ የተከበበ ሳይሆን ባኅጢአተኞችና በቀራጮች የታጀበ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን የራሱን ኢምፓየር የሚገነባና ስሙን የሚተክል ሳይሆን ለእግዚአብሔር መንግስት የሚሮጥና በመንግስቱ እሴተ-ስርዓት የሚገዛ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በስሪ-ፒስ መድረክ ላይ የሚምነሸነሽ ሳይሆን ትህትናን እንደ ልብስ የለበሰና የዋህ የሆነ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በመድረክ ትወናው ደክሞት ላቡን መጥረጊያ ጨርቅ የያዘ ሳይሆን እግር ማበሻ ፎጣ የያዘ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም የሚነግድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስም የሚያገለግልና ለእግዚአብሔር ስም ክብር የሚሰጥ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ካጣ ከነጣው የሚመነትፍ ሳይሆን ለሌለው የሚያካፍል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን የራሱን ፈቃድ በማድረግ የተጠመደ ሳይሆን "ፈቃድህ ትሁን" ብሎ የሚያስተምርም የሚኖርም፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሚሰለጥን ሳይሆን ለሕዝቡ ጥቅምና እድገት የሚለፋ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ከኋላ ሆኖ ሕዝቡን የሚያስበላ ሳይሆን ከፊት ሆኖ ደጀን የሚሆን፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን እርሱ ዋናውን በልቶና ጠጥቶ ለሕዝቡ መናኛውንና ትርፍራፊውን የማያድል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ሕዝቡን የሆነ ቦታ ለመድረስ መነሻ ያደረገ ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ መዳረሻው የሆነለት፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ሁለቷን አሳና አምስቷን ቂጣ የቀደመ ብሎ የሚጎርስ ሳይሆን ለሕዝቡ እንድትሆን የሚያካፍል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በገንዘብና በራስ ፍቅር የተነደፈ ሳይሆን ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ፍቅር የተሸነፈ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ሕዝቡ ውስጥ እንዴት አድርጌ ራሴን ልትከልባቸው ብሎ የሚጨነቅ ሳይሆን "ክርስቶስ እስኪሳልባችሁ ድረስ ምጥ ይዞኛል" የሚል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ጎልያድ ሲመጣ ሕዝቡን ጥሎ የሚፈረጥጥ ሳይሆን በተግዳሮት ፊት እግዚአብሔርን ታምኖ ለሕዝቡ ዘብ የሚቆም፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ጥሪ አለኝ ብሎ ኪሱ ሲሞላ "አዲዮስ" የሚል ሳይሆን ጥሪው የማያረጅበትና በጥሪው ጸንቶ የሚቆም፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ለማንኛውም ብሎ ባጣ ቆየኝ የደበቀ ሳይሆን በሙሉ ልቡ እግዚአብሔርን አምኖና ታምኖ ሕዝቡን የሚያገለግል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ትምህርት እምቢ ስላለውና ንግድ ስለፎረሸበት ሳይሆን በእውነት የተጠራና ለጥሪውም ዋጋ የሚከፍል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን ከሰው ወይም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የሆነ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን እንደ አቤሴሎም የሚፈልገውን እስቲያገኝ ድረስ በር ላይ ቆሞ ወጪ ወራጁን የሚስም ሳይሆን ያለምንም ድብቅ አጀንዳ ብድራቱን ከእግዚአብሔር ብቻ ጠብቆ የሚያገለግል፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን በዛሬ ብቻ የታወረ ሳይሆን ዛሬ ላይ ሆኖ ነገ የሚታየው፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን የከተማ ዜንጦ ሳይሆን አፍጋኒስታንም ቢሆን ለመሄድ የተዘጋጀ፡

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን አለም-አቀፋዊ ሳይሆን እዛው ባለበት አራት በአራት ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ፡ ሎካሉም በሆነልን እንኳን ኢንተርናሽናሉ።

ባለ ራዕይማ ይፈለጋል፤
ነገር ግን . . . . . . . .

ይልቃል ዳንኤል
@nazrawi_tube