Get Mystery Box with random crypto!

ቤተክርስቲያንን እያደከሟትና በክርስቶስ በተገለጠው ህይወትና ተልእኮ ልክ እንዳትሆን ያዘገዩአት በው | ናዝራዊ Tube

ቤተክርስቲያንን እያደከሟትና በክርስቶስ በተገለጠው ህይወትና ተልእኮ ልክ እንዳትሆን ያዘገዩአት በውስጥና በውጪ የሚነሱ ኑፋቄዎች ብቻ ሳይሆኑ በክርስቶስ በተገለጠው ብርሃን የታየውን የቤተክርስቲያን ማንነትና ተልእኮ በሚገባ ያላዩ ነገር ግን መድረኮቻችንን በስፋት የያዙ ሰባኪዎች ስብከቶች ናቸው። ከአሳቤ ጋር ላትስማሙ ትችላላችሁ። ነገር ግን እንደ ስህተትና ኑፋቄ የማይቆጠሩ ነገር ግን በሰው አሳብ የተቃኙና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተደገፉ "ጥሩ ስብከቶች" ቤተክርስቲያንን ከልኳ አውርደዋታል። መልኳ እንዳይታይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ለምን ግን ክርስቶስን ማዕከል ያደረጉ ስብከቶች ጠፉ? ለምን ግን መሲሃዊ ማህበረሰብ መፍጠር አቃተን? ለምን ግን በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን ክብር ማየት ተሳነን? ለምን ግን ሙሴ በሰማይ ያየውን በጥንቃቄ ወርዶ እንደሰራ የራሱን መልካም አሳብ እንዳልጨመረበት በተገለጠው በክርስቶስ ልክ ለመስራት አቃተን? ወደ አዲስ ኪዳን ተመልሰን ክርስቶስን ካላገኘነውና በእርሱ አእምሮ ካላሰብን በስተቀር ክርስቲያናዊ ማንነትና ተልእኮ ሊኖረን ከቶ አይቻልም። ስመጥር ስለሆንን በየቦታው ስለተጋበዝን ይህንን የልክነት (የመሲሃዊ አገልጋይነት) ሚዛን ካደረግን ተሳስተናል። በአንድ ስብከት ከመድረክ መድረክ መዞር (ለቀማ ይሉታል!!!) ቤተክርስቲያንን ማገልገል ከመሰለን ተሳስተናል። ልኩ ክርስቶስና በእርሱ የተገለጠው የእግዚአብሔር የፈቃዱ ዕውቀት ብቻ ነው። እግዚአብሔር አሳቡን የነገረን በልጁ ነውና ልጁ በሌለበት ስብከት የልጅነት ህይወት አይታሰብም። አንድም ቀን ብትሆን ክርስቶስን እናውራ እንስበክ። የራሳችንን የንግግር ችሎታ የጥበብ ብልጫ ትተን በክርስቶስ ላይ እናተኩር።

የሰው ስብከት የሰው ጥበብ የሰው ንግግር የሰው ችሎታ የሰው ምኞት በበዛበት ማህበር መካከል ከክርስቶስ በቀር ላለማየት ላለማወቅ መቁረጥ በክርስቶስ አእምሮ መገኘት ነው። ጥበብ ይህ ነው። የመንፈሳዊ አገልግሎት ከፍታው ይኼ ነው። የአገልግሎት መዘወሪያውና ጽኑ መሰረቱ ይኸው ነው።

ባለቴሌቪዥን ሰባኪዎችማ ከዚህ እሩቅ ናቸው። እነሱን ማሳመንና ርቀው ከሄዱበት መንገድ መመለስ አይቻልም። ስብከታቸውና ትምህርታቸው ከክርስቶስ (our new center of consciousness) በብዙ የራቀ ነው።

No Christological mind, No Christological Community.
No Christ like mind, No Christ like living.

@nazrawi_tube