Get Mystery Box with random crypto!

“በስውር…” የተረሳ ወይስ የተጣሰ? “በስውር…” መረሳትም መጣስም የሌለበት ቃል ነው። በክር | ናዝራዊ Tube

“በስውር…”

የተረሳ ወይስ የተጣሰ?

“በስውር…” መረሳትም መጣስም የሌለበት ቃል ነው። በክርስቶስ ትምህርት መሠረት በስውር መፈጸም አለባቸው የተባሉት ሦስቱ ነገሮች አሉ:-

1. ስንሰጥ በስውር መሆን አለበት። “… በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።”(ማቴ.6:3-4)

2. ስንጸልይ በስውር መሆን አለበት። “… በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” (ማቴ.6:6)

3. ስንጦም በስውር መሆን አለበት። “… በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” (ማቴ.6:17-18)

እነዚህ በስውር ተፈጽመው ግልጽ ክፍያን የሚያገኙ ክርስቲያናዊ ተግባራት ናቸው።

ስንመጸውት፣ ስንጸልይና ስንጾም ሰዎች “ፐ” እንዲሉን መሆን የለበትም። ለሰዎች ከመታየት ፍላጎት ጋር የሚደረግ የትኛውም መንፈሳዊ ተግባር ውድቅ ነው። በፊታችን መለከት ለማስነፋት የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የከበሩ አይደሉም። በዚህ ዘመን መንፈሳዊ ተግባሮቻችንን እያዝረከረከ ከንቱም እያደረገ የሚገኝ ነገር ቢኖር “ግብዝነት” የሚባለው ነገር ነው። በምኩራብም ሆነ በመንገድ አንድን ነገር ልናደርግ ስንነሳ የሚቀሰቅሰን ኃይል ወይም የተነሳሽነት አቅም የምናገኘው ከልታይ ባይነት ከሆነ ግብዝነት ማለት እሱ ነው። ግብዝነት ደግሞ በሰማያት ባለው አባታችን ዘንድ ያለንን ዋጋ ያሳጣል። እንደ ግብዞች አት ሁን የሚለው መመሪያ ነው።

ስንመጸውት፣ ስንጸልይና ስንጾም እግዚአብሔር በስውር የተደረገውን የሚያይ በግልጽም የሚከፍል መሆኑን ከማመን ጋር መሆን ይኖርበታል። ከሰዎች ከምናገኘው የአድናቆት ክፍያ ይልቅ የእግዚአብሔር ክፍያ ይሻላል ብሎ የሚያስብ አማኝ ሁሉ እነዚህን መንፈሳዊ ተግባራት በስውር መፈጸም ይጠበቅበታል። በነዚህ ክፍሎች “በስውር የሚያይ አባትህ በግልጽ ይከፍልሃል” የሚለው ሃሳብ ሁለት ነገሮችን ይዟል። አንድም እግዚአብሔር የተሰወረውን የሚያይ መሆኑን ሲሆን ሌላም እግዚአብሔር በግልጽ ከፋይ መሆኑን ነው። አቤት ትጋቱ፣ አቤት ልገሳው፣ አቤት መሰጠቱና መሥዋዕትነቱ የመባል ፍላጎታችንን ገታ አድርገን በስውር አይቶ በግልጽ በሚከፍል አባታችን ፊት ዋጋ በሚኖረው ሁኔታ ማድረግ ይኖርብናል።

በዚህ ቃል ሚዛን ላይ ስንወጣ እንዴት ነን? ትንሽ የምትሉት ይኖራችኋል? እኔ ይህ ቃል የተረሳ ወይም የተጣሰ መስሎኛል።

ወርቅነህ ኮይራ
@nazrawi_tube