Get Mystery Box with random crypto!

˙ ትንሽ ስለ “ሪቫይቫል” መቼም በራሱ በእግዚአብሔር ህልውና፣ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ | ናዝራዊ Tube

˙ ትንሽ ስለ “ሪቫይቫል”

መቼም በራሱ በእግዚአብሔር ህልውና፣ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እርሱ በተዘከረው እውነት እንዲሁም በሰው ልጆች ታሪክ መካከል ጣልቃ እየገባ ራሱን ያለምስክር እንደማይተው የምናምን ከሆነ በሪቫይቫል አለማመን አንችልም።

ሰሞኑን ከአዝበሪው ዩኒቨርሲቲ ሪቫይቫል የተነሳ የተለያዩ ምልከታዎች ሲሰነዘሩ ማስተዋል ችለናል፡ ይሄ ትክክል ነው ያኛው ደግሞ ስሁት ነው ወደሚለው ፍረጃ ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ ባይሆንም በኔ ግምት መንፈሳዊ መነቃቃትን አስመልክቶ ልንጋፋቸው የማይገቡን ጥቂት ነጥቦች ያሉ ይመስሉኛል፡፡

~ ፩ ~

አንድ ሰው፣ ወይም አንድ አጥቢያ ቤተክርስትያን፣ ወይም የአንድ ዘመን አማኞች ሪቫይቫል መናፈቃቸው በራሱ የሆነ ነገር ትክክል አለመሆኑን ወይም የሆነ ነገር እንደ ጎደላቸው የሚጠቁም ምልክት ነው፡ በታሪክ ውስጥ የተከሰቱትን፣ ወይም አሁን እየሆነ ካለው “የአዝበሪው መነቃቃት፣ ካልሆነም በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር በሰዎች መካከል ያደረገውን ጉብኝት በማስተዋል ያንን አሁንና እዚህ እንዲሆን መናፈቅ ቢያንስ ቢያንስ አሁን በያዝነው ነገር አለመርካታችንንና ሌላ የምንራበው ነገር እንዳለ የሚያስረዳ ነው፡ ይሄ ደግሞ ፍጹም የጤነኝነት ምልክት እንጂ የመታመም ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡ የጤና-ቢስነት ምልክት ሊሆን የሚችለው እንደዚህ አይነት ርሃብና ናፍቆት ባይኖር ነበር።

ውሃ ጠጥቶ ወዲያው “ድገሙኝ” የሚል ሰው ገና እንዳልረካ ነው የሚያሳየው እንጂ መታመሙን አይደለም፡ እንዲሁም ሪቫይቫልን መናፈቅ የሆነ ነገር እንደጎደለን ከማሳየቱ ባሻገር ፍጹም የሆነ የጤንነት ማረጋገጫ ነው፡ ካልጠማን ወይም ካልራበን እንፍራ ምክንያቱም በዚያው ይዞን ሊሄድ ይችላልና።

~ ፪ ~

ሪቫይቫልን ፈጽሞ የምንኮርጀው ወይም የምናስመስለው ጉዳይ አይደለም፡ በቅዱሳን ሕብረት ውስጥ ብዙ ነገር ማስመሰል ይቻላል፡ ስብከትን፣ መዝሙርን፣ ጸሎትን እንዲሁም ሌሎች ሌሎችን፡ መንፈሳዊ መነቃቃትን ግን ፈጽሞ ማስመስል አይቻልም፡ ምክንያቱም ሪቫይቫል ከንግግር፣ ከመዝሙርና ከስብከት በተለየ መልኩ ሰፊ ወደ ሆነ የሕይወት ለውጥና ጥልቅ ወደ ሆነ እግዚአብሔርን ወደ መፍራት መንገድ ይመራልና፡፡

ሪቫይቫል “የመልካም ወጣት” ፕሮግራም አይደለም።

እግዚአብሔር ቸብ ቸብ አድርጎ ወይም እንደ ጠበል ረጨት ረጨት አድርጎን ሊያልፍ ሳይሆን የሚመጣው ሰዎች ያረከሱትን ስም ለመቀደስ የጣሉትን ክብር ደግሞ ለማንሳትና እርሱ ወደሚፈልገው የሕይወት ቀጠና ለማስገባት ነው፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የሚኮረጅ መነቃቃት የለም፤ አይሄድ አይመጣ በሆነ መልኩ የሸመደድነው ሪቫይቫል ካለ ሲጀምርም ሪቫይቫል አልነበረም ማለት ነው፡ እንደ ግብጽ ጠንቋዮች የተወሰነ መንገድ ሙሴን ልናስመስለው እንችል ይሆናል ነገር ግን መጨረሻ ላይ እባባችን በሙሴ እባብ መዋጧ አይቀሬ ነው።

~ ፫~

ሪቫይቫል ፈጽሞ እኛ በምንጠብቀው መንገድና መለኪያ ይመጣል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለብንም፡ ሪቫይቫል ፈልገንም፣ የሚመጣበትንም መንገድ ወስነንም አይቻልም፡ በሪቫይቫል ወቅት የመነቃቃቱ ባለቤት “ይቀበሉኛል ወይስ አይቀበሉኝም” የሚል ሥሌት ውስጥ ከማንም ጋር አይገባም፡ ጥጉን ይዘን ስንፈላሰፍበት እንከርማለን እንጂ እግዚአብሔር ማናችንንም ሪቫይቫል ስለመሆኑ ለማሰመን ጊዜ አያጠፋም፡ በዋነኘናት ሲጀምርም ስለ እኛ ስይሆን ስለ ስሙ ነው፡ በመጽሃፍ ቅዱሳችን ውስጥም ይሁን እንዲሁም በታሪክ ውስጥ በእግዚአብሔር ስራ ላይ “ሲፈላሰፉ” ራሱ እግዚአብሔር ያመለጣቸውና ጥጋቸውን እንደያዙ የቀሩ ሰዎች አሉ፡ ልክ ያ ንጉሱ ይደገፈው እንደነበረው አይነት ሰው ማለት ነው፡ “በውኑ እግዚአብሔር የሰማይን መስኮት ቢከፍት ይህ መሆን ይችላልን?” ብሎ አለ፡ አርቆ ማሰቡ ነበር፡ ነገር ግን የሰማይና የምድሩን ጌታ እየወሰነው እንደሆነ አላስተዋለም ነበር፡፡

እግዚአብሔር በእውነት በሚሰራበት ወቅት የሚያዋጣው ብዙ ማውራቱና መፈላሰፉ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ በአንድ መሰመሩ ነው፡፡

አዕምሮአችንን ጥለን ዝም ብለን መጋለብ ባይገባንም እግዚአብሔር ስራ ሲሰራ ግን ጥጉን ይዘን በሚጢጢዬ አዕምሮአችን ተፈላስፈን ከጨርስን በኋላ አይደለም የምንቀላቀለው፡ የሚገርመው ሪቫይቫሉ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ሁሉ በአዕምሮአችን ብንመራመርበት መልስ ላናገኝለት ሁሉ እንችል ይሆናል፡ በእንደዚህ አይነት ወቅት ከፍልስፍናው ይልቅ እግዚአብሔር እንዲረዳንና ማስዋልን እንዲሰጠን መጸለዩ ብቻ ነው የሚያዋጣው፡ አለበለዚያ ከእግዚአብሔር ጋር መሸዋወድ ሁሉ ይቻላል፡ ይሄንን ልብ እንበል፤ እግዚአብሔር እኛ ልንቀበለው ወይም የስነ-መለኮት ሳጥናችንን ሊሞላ በሚችል መልኩ ብቻ ይመጣል ብለን ካሰብን ከሪቫይቫሉ ባለቤት ጋር የመተላለፍ በሩ ሰፊ ሊሆንብን ይችላል፡ እግዚአብሔር ከሳጥናችን የሚያልፍ ነገር ሊያደርግ ይችላል፡ ስለዚህ ጉዳዩ ቀመራዊ ሳይሆን “መንፈሳዊ” ብቻ ሊሆን ይችላል።

~ ፬ ~

ሪቫይቫልን ስናስብ የሆነ ሙታን ከመቃብር እየተጎተቱ ሲወጡ፣ እውራን ሲበሩና አንካሶች ሲዘሉ ብቻ አድርገን ማሰብ የለብንም፡ የመንፈሳዊ መነቃቃት ትልቁ አላማ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ከልባቸው በመውቀስ ንስሃ እንዲገቡ ማድረግና እግዚአብሔርን ወደሚመስል ሕይወት መጥራት ነው፡ በሪቫይቫል ወቅት እግዚአብሔር ታላላቅ ድንቅና ታምራትን በማድረግ ሰዎችን የማስደመም አባዜ የለበትም፡ በአብዛኛው ወቅሶና አሳምኖ እንጂ አስደንቆና አስገድዶ አይደለም የሚለውጠው፡ ጉዳዩ የ impression ሳይሆን የ conviction ነው።

ስለዚህ አንዳንድ እኛ የሪቫይቫል መለኪያ ብለን ያስቀመጥናቸው ወይም የምናምናቸው ነገሮች ባይኖሩም እንኳን ነገርዬው እግዚአብሔር ሊኖርበት ይችላል፡ ከላይ እንዳልነው ቁም ነገሩ እኔ እቀበለዋለሁ ወይስ አልቀበለውም የሚለው ሳይሆን እግዚአብሔር የሚመጣበት መንገድ ነው፡ ሲጀምር እኔ ማን ነኝ?!

~ ፭ ~

ሪቫይቫልን የልብ እንጂ የቦታ ጉዳይ አድርገን ማሰቡ ያን ያህልም ተገቢ ላይሆን ይችላል፡ እንኳን መቶ ሰው አይደለም የዓለም ሕዝብ እንዳለ አዝበሪ ቢመጣ ምንም ሳይሆን እንደመጣ በዛው ሊመለስ ይችላል፡ አዝበሪ ስለሄድን የሚወድቅብን መንፈስ እንዳለ አድርገን ማሰብም አግባብነት ላይኖረው ይችላል፡ እዛው አዝበሪ ቻፕል ከነበሩት ውስጥ ስንቶቹ “ተነኩ” ወይም የሪቫይቫሉ ተጽዕኖ አገኛቸው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ይመስለኛል፡ ለምሳሌ ያህል ከወጡት ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደምናስተውለው እዛው ስብስብ ውስጥ የሚያለቅሱትና “የሚዘሉት” ጥቂቶች እንጂ አብዛኛው ሰው እጁን አጣምሮ ነበር የቆመው፡ ለምን እነዚህኞቹ ዘለሉና አለቀሱ እነኛዎቹስ ለምን አልዘለሉምም አላለቀሱምም የሚለው ክርክር ውስጥ ለመግባት ሳይሆ እዛው አዝበሪ ቻፕል ውስጥ ተገኝቶም እንደነበራት ሆኖ ወደቤቱ የሚመለስም አይጠፋም ለማለት ያህል ነው፡ የሚያዋጣው አዝበሪ ድረስ ለመሄድ መናፈቅ ሳይሆን ( መሄድ በራሱ ምንም ክፋት የለውም ) እዛው ያለንበት ቦታ እግዚአብሔር እሳቱን እንዲጥል መንበርከኩ ነው፡፡

የአዝበሪው ጌታ የሁሉ ጌታ ነው።