Get Mystery Box with random crypto!

አዳምን ኤደን ገነት ውስጥ ከእግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ ውጭ ሊያነቃው የሚችለው አቅም አልነበ | ናዝራዊ Tube

አዳምን ኤደን ገነት ውስጥ ከእግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ ውጭ ሊያነቃው የሚችለው አቅም አልነበረም: አዳም ኤደን ገነት ውስጥ ፈፅሞ በራሱ መንቃት አይችልም ነበር: የግድ ከእርሱ ቁጥጥርና እውቅና ውጭ የሆነ እስትንፋስ በአፍንጫው ሊገባበት ያስፈልገው ነበር::

ሰውን ማንም ሰው በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት አያነቃውም: ማናችንም ማንንም በሚያማምሩ ስብከቶቻችንና የትወና ብቃታችን ከተኛበት ጥልቅ እንቅልፍና ድንዛዜ ማባነን አንችልም: የእግዚአብሔር እስትንፋስ ግን ይችላል::

ሁልጊዜ እውነተኛ መንቃት እግዚአብሔር ራሱ በሚጭረው እሳት የሚመጣ ነው: በናዳብና በአብድዩ እሳት አይደለም: ማናችንም እሳት አናዋጣም: እሳቱን የመጠበቅ ግዴታ ግን አለብን::

እግዚአብሔር እርሱ በፈለገው ቦታና የታሪክ ፍሰት መሃል የሰው ልጅ ፈጽሞ በፖለቲካና በሃይማኖት ሊያመጣው የማይችለውን መለኮታዊ ጉብኝት ወይም ጣልቃ ገብነት ያመጣል።

ሰው ሁሉ ቀልቡ በሌላ ነገር በተወጠረበትና ርሃብና ጥማቱን ለማስታገስ ውሃ ሊይዙ የማይችሉትን ጉድጓዶች በሚቆፍርበት አንድ የታሪክ አንጓ ላይ የታሪክ ባለቤትና ጠቅላይ የሆነው እግዚአብሔር የሆነ ቦታ በለሆሳስ ነገር ግን ለሁሉ በሚሰማና ሊደበቅ በማይቻል መልኩ ይናገራል፡፡

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በፈለገው ሰአትና ቦታ ጣልቃ መግባት የሚችለው እግዚአብሔር ባልጠበቅነው ቦታና መንገድ ራሱን በመግለጥ ባዶ ሆነው ነገር ግን የምንመጻደቅባቸውን ማድጋችንንና ኮሮጆአችንን ያስጥለናል፡ እንዲህም በማድረግ ወደማይነጥፈውና ወደማይደርቀው የራሱ ባህርና ወንዝ ይጋብዘናል፡ እርሱ ራሱ ወንዝ እርሱ ራሱ ባህር ይሆነናል።

ጭው ባለው ምድረ በዳችን ላይ ርጥበት ይለቅበትና ጽጌሬዳ እንዲያበቅል ያደርገዋል።

ከኛ እንዳልሆነና የጽድቃችን ውጤት አለመሆኑን ለማሳየት እርሱ ራሱ ሞት፣ ጭንገፋና፣ ድርቀት በነገሰበት ሰፈራችን ሕይወትን፣ ፍሬአማነትንና፣ ልምላሜን ይልክበታል - ስለ ራሱ እንጂ ስለ እኛ ግን አይደለም።

እንጸልይ፦
አቤቱ ሕይወታችን ከማይነጥፈው ከአንተ ሕይወት ይቀዳልና አትተወን፡ አቤቱ አቁማዳችንና ጉድጏዶቻችን ነጥፈዋልና እንደገና ሙላቸው: ሕይወትህ - የራስህ ሕይወት በመካከላችን ይፍሰስ፡

አቤቱ ስለ እኛ አይደለም ስለ ታላቁ ስምህ እንጂ።

. . . አንተ አይደለህምን?!

ይሉ ዳኑ
@nazrawi_tube