Get Mystery Box with random crypto!

በKentucky ግዛት Lexington ከምትባል ከተማ ሃያ ማይል ያህል ርቃ የምትገኝ ትንሽ የመንደ | ናዝራዊ Tube

በKentucky ግዛት Lexington ከምትባል ከተማ ሃያ ማይል ያህል ርቃ የምትገኝ ትንሽ የመንደር ከተማ ነች Wilmore. ከተማዋን ከተማ ያደረጋት ግዙፍ የክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ Asbury University እና Asbury Theological seminary ነው ማለት ይቻላል። የመማሪያ ሕንጻዎች፣ ላይብሬሪዎች፣ ቢሮዎች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የተማሪ ማደሪያዎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች ለዚያች የመንደር ከተማ ውበት ሆነዋል። ለቀጣይ ትምህርቴ ያንን ግቢ ከረገጥኩ ገና ዓመት አልሞላኝም። ለጸሎት የሚሰጡት ትኩረት፣ ለግል የጥሞና ጊዜ፣ ለጋራም አምልኮ ያላቸው ትርጉም ከፍተኛ ነው። ትምህርት ቤቱ የዌስሊ አሻራ ያለበት መሆኑንና አንዳንዶቹ መንፈሳዊ ልምምዶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከመሆናቸው ባሻገር እንደ ዌስሊ ለጋሲ እንደሚታዩ ሰምቻለሁ።

ባለፈው ሳምንት የተለመደው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቻፕል (ሳምንታዊው የማለዳ ጸሎት) በሚደረግበት ወቅት ያልተጠበቀ መለኮታዊ መገኘት በመካከላቸው መከሰቱንና እንግዳ ነገርም ሆኖ እንደነበር በበቀደሙ ልጥፌ ነግሬያችሁ ነበር። የ አሜሪካ ቤተ ክርስቲያን ደክማለች ለዓለማዊነት እጇን ሰጥታለች በሚባልበት፣ ሠይጣን በምድሪቱ ላይ ዙፋኑን ዘርግቶአል ትውልዱን በልቶታል ተብሎ በሚወራበት፣ ክፋትና ርኩሰት ጣራ ነክቶአል ወንጌልን መስበክ ነውር ሆኗል ግለኝነትና ቁሳዊነት ምድሪቱን ወርሷል፣ ትውልዱም ከሃዲዱ ወጥቶ ወደ ሞት እየተነዳ ነው በሚባልበት በዚህ ጊዜ ተስፋን የሚያጭር ነገር በዩኒቨርሲቲው ቻፕል ውስጥ ተከስቷል።

ዛሬ ዓይኖቼ ያዩትን ከጓደኞቼም ስለሁኔታው የሰማሁትን ልመስክር። “አቤቱ፥ ትመለሳለህ ታድነንማለህ፤ ሕዝቡም በአንተ ደስ ይላቸዋል።” (መዝ. 85:6) ይኼውላችሁ:- እገሌ የሚባል ታዋቂ አገልጋይ ይመጣል ተብሎ አልታወጀም። የማነቃቂያ ኮንፈራንስ አለ ተብሎ ማስታወቂያ አልተለጠፈም፣ አልተለፈፈም። ዕቅድ ተይዞ፣ ስልት ተነድፎ ምንም ዝግጅት አልተደረገም። ጥቂት የአምልኮ መሪዎች ዝማሬያቸውን አቀረቡ… የተለመደው ዓይነት አጭር የቃል መልዕክት ተላለፈ፣ ከመልዕክቱ በኋላ በቃሉ የተወቀሳች ሁ ወደፊት ኑ ጥሪ ቀረበ፣ ጸሎት ተጀመረ ዝማሬው ቀጠለ፣ ንስሓ መግባት ምስክርነት መስጠት ሆነ አልቆም ብሎ ይኼው ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። መች እንደሚያቆም የሚያውቅ ሥጋ ለባሽ የለም። እሳቱ እንደ ነደደ ነው።

ይነጋል ይመሻል ያለማቋረጥ ይመለካል፣ ይጸለያል፣ ቃል ይነበባል፣ ንስሓ ይገባል፣ ምስክርነት ይተላለፋል። የሙዚቃ ድምቀት የለም። የመዝሙር ውበት የድምጽ ውህደት ለረጅም ጊዜ ሲያጠኑ የቆዩ መዘምራን የሚዘምሩ ይመስላል። የክብሩ ሙላት አለ። ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ ሰዎች በሠልፍ ወደ አዳራሹ ይገባሉ። ዝናብ ብርድ ጨለማ የማይበግረው ረሃብተኛ ሕዝብ በክብሩ ጥማት የተጎዳ ትውልድ በአዳራሾች በራፍ ይንገበገባል። የክብሩ ብርሃን ቤቱን ሞልቶአል። እንደ ወትሮው ፕሮግራም መሪ ተነስቶ “ከዚህ ቀጥሎ ይህና ያ ይሆናል” የሚልበት ዓይነት formal አካሄድ የለም። መንፈስ እንደ መራው አንዱ ተነስቶ የመጣበትን ግዛት ጠቅሶ ከቃሉ አንድ ክፍል አንብቦ ይወርዳል። ሕዝቡ ያንን የቃሉን ክፍል በዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሰማ ሰው በመደነቅ ይሰማል። የገንዘብ ማሰባሰብ የሌለበት፣ ታዋቂና ታላላቅ ሰባኪዎችና ዘማሪዎች ያልተጋበዙበት፣ የሙዚቃ ግርግርና የመድረክ ድምቀት የማይስተዋልበት፣ የማስታወቂያ የፖስተርና የካሜራ ግርግር የማይታይበት የተለመደው የፕሮግራም አካሄድ ሥርዓት የማይነበብበት፣ የመንፈሱ የበላይነት ብቻ የክርስቶስ ማዕከላዊነት ብቻ የተጠበቀበት ሪቫይቫል ነው።

አራት ትላልቅ አዳራሾች በሰው የተሞሉ ናቸው። ሁሉም ጋ ጸሎት አለ፣ ንስሓ አለ፣ የቃል ንባብ አለ፣ ምስክርነት አለ፣ ዝማሬ አለ፣ ማልቀስ አለ፣ እንደ ምርኮኛ እጅ ወደ ላይ አንስቶ ወደ መድረክ እየተመሙ መምጣት አለ፣ እጅ መጫን አለ። ወንድሜ ፋሲል አረጋ ቅድም ሲነግረኝ “በነዚህ ቀናት ውስጥ ወደ ጉባኤው ገብቼ ሳላለቅስ የወጣሁበት ጊዜ የለም” ነበር ያለኝ። እኔም ያንን ነገር አይቻለሁ። ቀስ ብዬ አጠገቤ የተቀመጠቺውን ባለቤቴን ሳይ ጉንጯ ርሷል። ወንድሜ ዶ/ር ተድላ ወልደዮሐንስ ከሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ ሃምሳ የሚያህሉ ወጣቶችን ከሌሎች ፕሮፌሰሮች ጋር ይዞ መጥቶ ነበር። ወጣቶች ውስጥ የተፈጠረው የጌታን ፊት የመፈለግ ልብ ይደንቃል። አሜሪካ ተስፋ አላት ያስብላል። ጌታ እንዲህ አለኝ የሚል ሰው እንደ ተንባይ የመሆን ዝማሚያ የሚታይበት ሰው አላየሁም ግን ቃሉ ሲነበብ ሕዝቡ የሚሰጠው ምላሽ ጌታ ራሱ የሕዝቡን ልብ ወደ ቃሉ መልሶት ካልሆነ በቀር ሊሆን የማይችል ነው።

በየመሃሉ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች እንደ አሥር ዓመት ሕጻን ሲፈነጩ ወዲያና ወዲህ በደስታ ሲወዛወዙ ይታያሉ። እጅግ ያስደስታል!! አንድ ቃል በተነበበ ቁጥር ከኋላ እየተምዘገዘጉ መጥተው ከመድረኩ ሥር ዘፍ ብለው የሚወድቁ ወጣቶችን ሳይ ልቤ በሐሴት ይሞላ ነበር። መድረኩን የያዙት በ አብዛኛው ወጣቶቹ ናቸው። መጋቢያን በዕድሜ ጠና ያሉት አስተናጋጅ ናቸው። አንድ ትልቅ ቤት ውስጥ ምግብና ውሃ ሞልቶ ነበር የራበው ወጥቶ በነጻ በልቶ ጠጥቶ ይመለሳል። የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ቤተ ክርስቲያን ተደገመች ብያለሁ። በተሳታፊዎች ፊት የሚነበበውን  ፍቅርና ፈገግታ እውነት ለመናገር አሜሪካ ከመጣሁ ጊዜ ጀምሮ አይቼ አላውቅም። መጸለይ ያለበት ነገር ምንድነው? 1. ይኼ ሪቫይቫል በወንጌል ምስክርነትና በክርስቶስ ተልዕኮ ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መሆን እንዲችል ጸሎት ያስፈልጋል። 2. የሰው እጅ ጣልቃ እንዳይገባ ታዋቂ ለመሆን ክብርንና ጥቅምን የሚፈልጉ ሾልኮ ገቦች ሪቫይቫሉን እንዳይጠመዝዙት መጸለይ አስፈለጊ ነው እላለሁ።

Workneh D. Koyera
@nazrawi_tube