Get Mystery Box with random crypto!

ሁለት ዓይነት ዐይኖች (ማቴ. 6፡22-23) የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ | ናዝራዊ Tube

ሁለት ዓይነት ዐይኖች (ማቴ. 6፡22-23)

የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!

በዚህ ክፍል ውስጥ (ቁ. 22–23) ያለውን ሀሰብ ከተገለጸበት አውድ ውጪ መረዳት በጣም አሰቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ክፍል የተከበበው ስለባለጠግነት በሚያወሩ ክፍሎች ነው (ከቁ.19-21 እና 24 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙት ὁ ὀφθαλμός . . . ἁπλοῦς ሚገኘው “ጤናማ ዐይን” እና ὁ ὀφθαλμός . . . πονηρὸς “ታማሚ ዐይን” የሚለው ሀረግ በቀጥታ የዐይንን ጤናማነት እና ታማሚነት የሚያመለክት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ይልቁንም በዚህ ክፍል ውስጥ ምሳሌያዊ ይዘት ያለው ነው፡፡

በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች አይሁዳዊያንንም ጨምሮ ዐይን እሳት ወይም ብርሃንን በውስጡ ይዟል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ሰዎች ማየት የሚያስችላቸው ይህ ብርሃን እንደሆነ ይታመን ነበር፡፡ ለምሳሌ ምሳ. 15፡30 “የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ . . .” ይላል፡፡ በዘፍ. 27፡1፣ 48፡10፣ ዘዳ. 34፡7፣ ሰቆ. 5፡7 ላይ ደግሞ ዐይን እንደሚጨልም ይናገራል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር የሰዎችን ዐይን እንደሚያበራ በዕዝ. 9፡8፤ 1ኛ ሳሙ. 1፡12፣ 1ኛ ሳሙ. 9፡8 ላይም መመልከት ይቻላል፡፡ በዚህ ሳያበቃ በብሉይ ኪዳን መጻሐፍት ውስጥ ዐይን እንደ ፀሐይ ብርሃንን እንደሚያፈልቅ የሚያሳዩ ክፍሎች አሉ (2ኛ ሳሙ. 12፡11፣ መክ. 23፡19 ይመልከቱ)፡፡ እንዲያው በአንዳንድ ክፍሎች ውስጥ ከዐይን የሚወጣው የብርሃን ጨረር በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ በግልጽ እንደሚታይ የሚናገሩ ክፍሎች አሉ (ዳን. 10፡6፣ ራዕ. 1፡14፣ 2፡18. 19፡12 ይመልከቱ)፡፡

በዚህ ክፍል ውስጥ “ታማሚ ዐይን” ተብሎ የተተረጎመው ὁ ὀφθαλμός . . . πονηρὸς ሀረግ በጥንት መካከለኛው ምስራቅ ባሕል መሠረት “ክፉ ዐይን” ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ አገላለጽ በጥንት መካከለኛው ምስራቂ ባሕል ውስጥ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በአይሁዳዊያን ባሕል ውስጥ ጨምር ውስጥም ነበር፡፡ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ማቴ. 20፡15 እና በማር. 7፡22 ላይ ተጠቅሶ እናገኛል፡፡ ትርጉሙም በሌላ ሰው ነገር የሚቀናን፣ የሰውን ነገር የሚፈልግ፣ ስግብግብ ወይም ስግብግብ ዐይን የሚል ትርጉም ነበረው፡፡

በክፍሉ ውስጥ ὁ ὀφθαλμός . . . ἁπλοῦς ሚገኘው “ጤናማ ዐይን” የሚለው አባበል ከὁ ὀφθαλμός . . . πονηρὸς “ታማሚ ዐይን” ጋር ተነጻጽሮ በመቅረቡ ምክንያት ትርጉሙም የታማሚ ዐይን ትርጉም ተቃራኒ ነው፡፡ ማለትም ቃሉ ከልግስና ጋር የተያያዘ መሆኑን መመልከት ይቻላል (ያዕ. 1፡5፣ ሮሜ. 12፡8፤ 911፣ 13 ይመልከቱ)፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቃሉ “ከአንድ ሀሳብ” ጋር የተያያዘ ትርጉም እንዳለው እና ለአንድ ዓላማ መሰጠትን የሚያመለክት መሆኑን ቃሉን ያጠኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በቁ. 24 ላይ የተገለጸው ሀሳብ ይህንን ትርጉም ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡ ስለዚህም “ጤናማ ዐይን” ያላቸው ለጋሾች (6፡22) ሲሆኑ “ታማሚ ዐይን” ያላቸው ደግሞ ለጋሾች አይደሉም/ ስግብግቦች ናቸው (6፡23 እና 20፡15 ይመልከቱ)፡፡ እነዚህ “ታማሚ ዐይኖች” ያላቸው የብልጽግናቸው ሎሌዎች/ ባሮች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሀብታቸውን ለራሳቸው የሚያከማቹት በምድር ላይ ብቻ ነው፡፡

ὁ λύχνος τοῦ σώματός ἐστιν ὁ ὀφθαλμός, “የሰውነት መብራት ዐይን ናት።” ይህንን ሀረግ አስመልክቶ የሥነ-መለኮት ምሁራን የተለያዩ አስተያየቶችን ተሰጥተዋል፡፡ በዋናነት ሁለት አመለካከቶች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ የመጀመሪያው አመለካከት “የሰውነት ብርሃን ዐይን ናት” ማለት ሰው ማየት የሚችለው በዐይኑ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም በቁ. 22ለ - 23ሀ ድረስ የተገለጹት “ጤናማ ዐይን” እና “ታማሚ ዐይን” ምሳሌያዊ አገላለጾች ናቸው፡፡ የደቀ መዛሙሩ “ጤናማ ዐይን”፣ ለጋስ ዐይን የብርሃን ምንጭ ሲሆን “ታማሚ ዐይን”፣ ቀናተኛ ዐይን የጨለማ ምንጭ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ጤናማ ዐይን ካላቸው በብርሃን የሚመላለሱ ሲለሚሆኑ ትክክለኛውን መንገዳቸው ያውቃሉ፣ የማያወላውሉ፣ ለአንድ ዓላማ የቆሙ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣብቀው የሚኖሩ ይሆናሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “የሰውነት መብራት ዐይን ናት” ማለት የሰው የውስጥ ማንነቱ መገለጫ መስኮት ዐይን ናት፡፡ አንድ ሰው ከገንዘብ ጋር ያለው ግንኙነት እርሱ በብርሃን ወይስ በጨለማ ውስጥ እንዳለ ያሳያል፡፡ ከእነዚህ ሁለት አመለካከቶች መካከል የመጀመሪያው ክፍሉ ከሚገኝበት አውድ ጋር አብሮ የሚሄድ ይመስላል፡፡ ይኼውም ይህ ክፍል የሚገኘው ኢየሱስ ስለ“ሚበልጥ ጽድቅ” ባስተማረበት አውድ ውስጥ ነው፡፡ ደቀ መዛርቱ ከገንዘብ ይልቅ እግዚአብሔርን የሚወዱ፣ ስግብግቦች ሳይሆን ለጋሶች፣ በሌሎች ሰዎች የማይቀኑ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ልሆን የሚችለው ስለእግዚአብሔር እና ስለመንግስቱ ትክክለኛ ጤናማ ዕይታ፣ ያልተንሸዋረረ ምልከታ ሲኖራቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ዐይናቸው “ጤናማ” ሲሆን ነው፡፡ ጠናማ ዐይን ካላቸው በብርሃን ይመላለሳሉ፡፡

በቁ. 23 ላይ የሚገኘው εἰ οὖν τὸ φῶς τὸ ἐν σοὶ σκότος ἐστίν , τὸ σκότος πόσον, “ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል።” የሚለው ሀረግ ደቀ መዛሙርቱ ስለሀበት ያላቸው ዕይታ የተበላሸ፣ የታመመ ከሆነ ሁለንተናቸው የታመመ እንደሆነ ያሳያል፡፡

በአጠቃላይ የማቴዎስ ወንጌል ጸሐፊ በዚህ ክፍል ውስጥ ὀφθαλμὸς ἁπλοῦς “ጤናማ ዐይን” እና ὀφθαλμὸς πονηρός “ታማሚ ዐይን” በሚሉ ሀረጋት አማካኝነት ያስተላለፈው መልዕክት እንደ አይሁድ ባሕል መሠረት የመጀመሪያው ለጋስ የሆኑ ሰዎች የሚያመለክት ነው፡፡ ማለትም ሀብትን ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ ጌታቸው ያደረጉ፣ መዝገባቸውን በሰማይ የሚያከማቹ ሰዎችን ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው ድግሞ ለጋስ ያልሆኑ፣ ስግብግብ ሰዎችን የሚያመለክት ነው፡፡ እነዚህኛዎቹ ሐብታቸው አምላካቸው የሆነባቸው፣ በምድር ላይ ሀብትን የሚያከማቹ ሰዎችን የሚያመለክት ነው።

Dr. Tekalign Duguma
@nazrawi_tube