Get Mystery Box with random crypto!

ከላይኛው የቀጠለ.... ገላ. 4፥8 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማ | ናዝራዊ Tube

ከላይኛው የቀጠለ....
ገላ. 4፥8 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ ገላ. 4፥8 በባሕርይ አምላክ አለመሆን ግልጽ ነው። ምንም አምላክ የለም፤ ከአንዱ በቀር። አምላክ ተደርጎ የሚመለክ የለም ማለት አይደለም። ግን ያ ጣዖት እንጂ አምላክ አይደለም። ወይም መለኮት አይደለም። እነዚህ ጣዖታት ፍጥረቶች፥ ፍጡራን፥ ወይም አጋንንት፥ ወይም የሰው እጅ ሥራ የሆኑ ቅርጻ ቅርጽ ናቸው እንጂ አምላክ ወይም መለኮት አይደሉም። በባሕርያቸው፥ በማንነታቸው ወይም በምንነታቸው አማልክት አይደሉም። ውስጣዊ፥ የራሳቸው የሆነ፥ ፍጥረታቸው የሆነ፥ አምላክነት የላቸውም።

ይህ φύσις የተባለው ቃል ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች ውስጥ ባሕርይ ተብሎ ሲተረጎም ወይም ሲሰኝ በተቀሩት ቃሉ በተጠቀሰባቸው ጥቅሶች በሮሜ 2፥27፤ 11፥21 እና 24፤ 1ቆሮ. 11፥14፤ ገላ. 2፥15፤ ኤፌ. 2፥3፤ ያዕ. 3፥7፤ ይኸው ተመሳሳይ ቃል (φύσις) በአማርኛ ፍጥረት እየተባለ ተተርጕሞአል። ፍጥረት ውስጣዊ ማንነት ነው። ባሕርይን በሚገባ ይገልጠዋል። ደስታ ተክለ ወልድ ባሕርይን ሲተረጕሙ፥ ‘ያልተፈጠረ፥ የማይመረመር፥ የማይታወቅ፥ ኅቡእ፥ ረቂቅ፥ ቅድስት ሥላሴን አንድ የሚያደርግ፥ በሥርው፥ በጕንድ፥ በነቅዕ የተመሰለ፤ የፈጣሪ ባሕርይ፤ አምላክነት’ ይሉታል። ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 162። ከላይ ባየናቸው ጥቅሶች ውስጥ ባሕርይ የሚለው ውስጣዊ ማንነት ወይም ኹነትን ነው።

ቀደም ሲል በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ሰብዕ፥ የባሕርይ ልጅ እና የጸጋ ልጅ የሚለውን ስንመለከት የባሕርይ ልጅ ሲባል ከአድራጊው ጋር አንድ መሆንን አመልካች ነው። ይህ ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የምንጠቀምበት የስነ መለኮት ቃል ወይም ሐረግ ነው። ባሕርይ የሚለው ቃል በአንዳንዶቹ φύσις የሚለው ቃል በተተረጎመባቸው ቦታዎች ተፈጥሮ ቢባልም፥ ለመለኮት ተፈጥሮ እንዳንለው ማሰብ አይመችም። ኢየሱስ ፍጡር አይደለምና የተፈጥሮ ልጅ አይባልም። ሥሪት እንዳይባልም እርሱ ሠሪ እንጂ ተሠሪ አይደለምና ይህም አያስኬድም። ኢየሱስ የባሕርይ ልጅ መሰኘቱ ወልድ እና አብ አንድ ባሕርይ ወይም በእንግሊዝኛ essence በግሪክ οὐσία ወይም ούσιος የተባለውን መሆናቸውንና የኒቅያው ጉባኤ አብ እና ወልድ አንድ ባሕርይ ὁμοούσιος ሆሞኡሲዮስ ወይም ὁμοούσιον ሆኖኡሲዮን መሆናቸውን ለመግለጥ እንደተጠቀመበት ተመልክተናል።

ቃሉ አንድ ዓይነትነትን ገላጭ ነው። ὁμός ሆሞ ወይም ሆሞስ አንድ ወይም አንድ ዓይነት ወይም ምንም ልዩነት የሌለው ተመሳሳይ፥ οὐσία ኡሲያ ባሕርይ። ይህንን ὁμοούσιος የሚለውን ሐረግ ወደ እንግሊዝኛ "consubstantial" ብለው ነው የተረጎሙት። ይህ የኒቅያ ጉባኤ አርዮስ የተወገዘበት ጉባኤ ነው። አርዮስ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ወይም እኩል ያልሆነ ከሰው የሚበልጥ ከአብ ግን ያነሰ ወይም ሙሉ መለኮት ያልሆነ ያደርገዋል። (አርዮሳውያን የሆኑ የዘመናችን የዋችታወር ተከታዮች ወይም የይሆዋ ምስክሮች ነን የሚሉ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ወይም እኩል ያልሆነ ከሰው የሚበልጥ ከአብ ግን ያነሰ ወይም ሙሉ መለኮት ያልሆነ የተፈጠረ ፈጣሪ ያደርጉታል።) ኋላ በ381ዱ የቁስጥንጥንያ ጉባኤም ይኸው መግለጫ ጸና።

ክፍል አምስትና የመጨረሻው ይቀጥላል።

ዘላለም መንግሥቱ
@nazrawi_tube