Get Mystery Box with random crypto!

የዛሬ 505 ዓመት፣ በዛሬዋ ዕለት፣ በኦክቶበር 31፣ 1517 አመተ እግዚ አንድ ብዙም የማይታወቅ | ናዝራዊ Tube

የዛሬ 505 ዓመት፣ በዛሬዋ ዕለት፣ በኦክቶበር 31፣ 1517 አመተ እግዚ አንድ ብዙም የማይታወቅ መነኩሴ በአንዲት ትንሽ የጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮፌሰር የነበረ ሰው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የቤተ ክርስትያን በሮች ላይ የተወሰኑ ወረቀቶችን ለመለጠፍ መዶሻ አነሳ። እነዚያን ወረቀቶች በቤተ ክርስትያን አደባባይ ላይ የለጠፈበት ምክንያት የቤተ ክርስትያኑ በር/አደባባዩ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንደ ማስታወቅያ ሰሌዳ ያገለግል ስለነበር በርከት ያለ ሰው እንዲመለከተውና ውይይት እንዲያጭር አስቦ ነበር።

በለጠፈው ወረቀት ውስጥ 95 አናቅጽት (Thesis) 'የኢንደልጀንስን' [indulgence] (የኃጢአት ይቅርታ ሰነድ) የመሸጥ ልምምድ ከጳጳሱ ፍቃድ ያገኘና አንድ ሰው 'ፑርጋቶሪ' [Purgatory] (ነፍስ ወደ ገነትም ሆነ ሲኦል ከመውረዷ በፊት የምትሆንበት ስፍራ) ውስጥ በምድር በሕይወት እያለ ስላጠፋው ስለሃጢያቱ የሚቆይበትን ጊዜ (ወደ መንግስተ ሰማይ ከመግባቱ በፊት) በሚገዛው 'ኢንደልጀንስ' መቀነስ ይችል ነበር የሚለውን ፀረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ የሚገዳደር ነበር። ይህ 'ኢንደንጀልስ' በወረቀት የሰፈረና የቤተ ክርስትያንን ይሁንታ አግኝቶ መግዛት ለቻለ ሁሉ የቀረበ ነበር። ህዝቡም ኢንደልጀንሱን ይገዛ ዘንድ 'በቅቤ አቅልጥ' ደላላ አሻሻጮች ይጎተጎት ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታዋን ሰጥታ ነበር። ህዝቡ ለራሱ፣ ለዘመዱና ለወዳጁ ይገዛ ነበር፤ በሞቱት ስም እንኳን ሳይቀር ይቸበችቡታል።

ሉተር 95 አናቅጽቱን ጽፎ ሲለጥፋቸው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባሉት ፕሮፌሰሮች መሃል ውይይት እንዲፈጥር በማሰብ ነበር። ነገር ግን ዘጠና አምስቱ አናቅጽት ከቪተንበርግ ፕሮፌሰሮች ከባቢ በዘለለ በመላው የጀርመን ግዛቶችና በጠቅላላው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ዘንድ ታላቅ ሁካታን ለመፍጠር በቃ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ህዝብ የዚህን መነኩሴ ስም ማወቅ ጀመረ፣ በቪተንበርግ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ዶክተሩን ማርቲን ሉተርን።

ህዝብን በማወክና ባለመታዘዝ ቤተክርስትያን ከሰሰቸው፣ በጀርመን ንጉስ ፊትም ራሱን እንዲከላከልና ያደረገው ሃሰት መሆኑን አውቆ እንዲያስወግድ ታዘዘ። ያደረገው ስህተት መሆኑን ባለመቀበሉና ህሊናው ለቅዱሳት መጽሐፍት ተገዢነታቸውን በማጽናቱ ምክንያት የውጤቱን ስሜት 500 አመታትን ተሻግሮ ዛሬ እኛም ይሰማናል።
.
«ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።»
.
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንዳሉት፣ "አሕይዎና ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠ ሥርዐት (Establishement) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው።" በዚህ ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በታማኝነት መታዘዝና መሰጠት ምክንያት የቤተክርስቲያን መልክ እንደ ቀደሞው ላይሆን ተለውጧል።
.
ተሐድሶ ብቻ መቆምን ይጠይቃል። ዘመንን መረዳትን፣ መጽሐፍትን መመርመርን፣ ለእግዚአብሔርና ለህሊናችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ተሐድሶ ወደ አባቶችና አያቶች ለመንፀሪያ መመልከትን አንደ ቄንጥ አያይም። የድነትን መኸከለኛ፣ የእምነትን ፈፃሚ፣ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ ትምሕርተ ክርስቶስን አደብዛዥን ሁሉ ለመቃወም ሁለቴ አያስብም። ተሐድሶ ቃለ–እግዚአብሔር ማሕደረ–ክርስቶስ በተባለችው ቤተክርስቲያን ሲደፈጠጥ ጥሪውን በማማ ላይ ያሰማል፤ እነሆኝ ለህሊናዬም ለቃሉም ቆሜያለሁ ይላል። እግዚአብሔር ልጁን በገለጠበት ቃል በኩል ለኅሊናዬ ብቻዬን እንኳን ቢሆን እቆማለሁ የሚል እውነትና ፅናት ያድለን።
.
የዛሬ 506 ዓመት ግድም የተለኮሰውን የተሐድሶውን እሳት ከሰሞኑ አስበን ውለናል። ከተሐድሶው ብቻዎች አንዱና የተሐድሶው ልበ ምት የሆነውን "ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ" የሚለውን ርዕስ አውስተናል።

መልካም እለተ ተሐድሶ ማስታወሻ! የከርሞ ሰው ይበለን!
አማኑኤል አሰግድ
@nazrawi_tube