Get Mystery Box with random crypto!

'መዳን ከእኛ ውጪ ነው ብሎ ማመን አስገራሚ ዜና ዓይደለምን?' ወንጌላዊው ክርስትና ከሌሎች 'ክር | ናዝራዊ Tube

"መዳን ከእኛ ውጪ ነው ብሎ ማመን አስገራሚ ዜና ዓይደለምን?"

ወንጌላዊው ክርስትና ከሌሎች "ክርስትናዎች" በእጅጉ የሚለየው ጽድቅ በእምነት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ጸጋ ለመሆኑ አጽንኦት በመስጠቱ ነው። ድኅነት "በጸጋ ብቻ"፣ "በእምነት ብቻ" የሚባለውም ለዚያ ነው። በእርግጥም ደግሞ ክርስቶስን ማወቅና በእርሱ ማመን የሰው ጥረት ውጤት ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚገኝ መለኮታዊ መገለጥ ነው። ቃሉን ሰምተን፤ መንፈሱን አግኝተን "እርሱ አምላኬ ነው በራልኝም!" የምንልበት የአብርሆት ቀን እስኪመጣ ነገር ሁሉ ድፍንፍን ያለ መሆኑንም ያለፉበት ያውቁታል።

ወንጌላዊውን ክርስትና ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየው ሌላኛው መታወቂያም "እምነት እንጂ ሥራ አያጸድቅም" በሚለው እወጃው ነው። መልካም ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሆኑ ቢታመንበትም ለጽድቅ ያግዛል ተብሎ ግን አይታሰብም። ወንጌላውያኑ አማኞች ፤ "ጽድቅ ከእኛ ውጪ ባለ ሌላ አካል (በክርስቶስ) ተሠርቶ አልቆ በጸጋ ገንዘባችን የምናደርገው፣ በእምነት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ውድ ስጦታ እንጂ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደሚሉት እግዚአብሔር በልጁ በሠራው የድኅነት ሥራ ላይ የእኛ መልካም ምግባር ተጨምሮ ምሉዕ የሚሆን ዓይደለም" ባዮች ናቸው።

በእርግጥም ደግሞ፣ ጽድቁ የእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር ከሆነ በእኛ ተጨማሪ ሥራ የምናሳካው ፣በጾምና በጸሎት ብዛት የምናሻሽለው ፣ በሂደት የምናዳብረው፣ በጊዜ ውስጥ አጎልብተን ወደ ፍጽምና የምናደርሰው ሰው ሰራሽ ጽድቅ አይኖርም። ጾምና ጸሎት ግን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። "ትቀደሱ ዘንድ ፈልጉ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ ማክበርና ራስ ወደሆነው ክርስቶስ ማደግ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ መልካም ፍሬ፣ ደግሞም የፍቅርና የልጅነት ግዴታ ቢሆንም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባው ግን ዕድገት ተለክቶና የቅድስና መጠን ታይቶ ዓይደለም። ነገሩ እንዲያ ቢሆንማ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ!

እነሆ በወንጌላውያኑ እምነት የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ አንድያ ልጁ በቀራኒዮ መስቀል ላይ "ተፈጸመ!" ባለ ሰዓት ፍጻሜውን አግኝቷል። ሥራው ጎልጎታ ጉብታ ላይ ተጠናቅቋል። በዚያ ላይ የሚጨመር ምንም ስለሌለም የዘላለምን ሕይወት የወረስነውና የምንወርሰው ገና ኃጢያተኞች ሳለን በተሠራልን ሥራ እንደሆነ መቁጠር ይቻላል። መጽሐፍም፣"ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧል" ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ይህ ጸጋ ኃጢያተኛውን ያለ ሥራ የሚያጸድቅ ስለመሆኑ ያወሳል። " ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና" ብሎ ይነግረናል።

በዚህ ላይ ከእኛ ውስጥ አፍልቀን የምንጨምረው፣ ይኼ ጎድሏል ብለን የምናሟላው አንዳችም የጽድቅ ሥራ የለም። የዛሬ 500 ዓመት ግድም ውስጡን ባላሳረፈው የጽድቅ ጥማት ሲሰቃይ የነበረውን መነኩሴና የሥነ መለኮት ኘሮፌሰር፣ ማርቲን ሉተርን ያስፈነደቀውም መዳን ከእኛ ውጪ ተሠርቶ ያለቀ መሆኑን መገንዘቡ ነበር። የዚህ ጽሑፌ ርዕስ ያደረግሁትም ይህንኑ የሉተር አባባል ነው። ይኼ እውነት ለገባቸውም የዜናው አስገራሚነት ሁሌም በልባቸው ይኖራል።

ሽመልስ ይፍሩ
@nazrawi_tube