Get Mystery Box with random crypto!

በቀጠናው የሚገኘው መከላከያ ሠራዊት እየወሰደ በሚገኘው ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ አሸባሪው ኦነግ ሸ | Natnael Mekonnen

በቀጠናው የሚገኘው መከላከያ ሠራዊት እየወሰደ በሚገኘው ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ አሸባሪው ኦነግ ሸኔ እየፈረሰ እንደሚገኝ ተገለፀ።

የደቡብ ዕዝ አንድ ኮር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ግርማ አየለ እንደገለፁት ሠራዊቱ በምስራቅ ጉጂና በምስራቅ ቦረና ዞኖች ህዝብን ሲያሸብር በነበረው ኦነግ ሸኔ ላይ በወሰደው ተከታታይነት ያለው ወታደራዊ እርምጃ በአንድ ወር ውስጥ ከ150 በላይ የቡድኑ ታጣቂዎች ለሰራዊቱ እጃቸውን የሰጡ ሲሆን ቡድኑ እየፈረሰ ይገኛል።

ኮሎኔል ግርማ የሠራዊቱን ብርቱ ክንድ መቋቋም ያቃተው ኦነግ ሸኔ በርካታ ታጣቂዎቹ በሠላማዊ መንገድ እጅ እየሰጡ መሆኑን አስታውሰው ፤ ቡድኑ ተደራጅቶ የመዋጋትም ሆነ የማድረግ አቅም እንደሌለው አብራርተዋል።

ሠራዊቱ የህዝባችንን አንድነትና ሰላም በሚያውኩ ፀረ ሠላም ሃይሎች ላይ እያስመዘገበ የሚገኘው ድርብ ድልና ስኬት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

የምስራቅ ጉጂ ዞን አስተዳደርና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቦጌ ታፈሰ በበኩላቸው ፤ ህዝባዊ መሰረት የሌለው የኦነግ ሸኔን እኩይ ተግባር የተገነዘቡ በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች የሠላም አማራጭን በመገንዘብ ለሠራዊቱ እጅ እየሰጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በተሳሳተ ትርክት የሸኔን ቡድን እንደተቀላቀሉ የሚገልፁት የሽብር ቡድኑ አባላት  ፤ የህዝቦችን ስቃይ ከማብዛት ውጭ ያገኘነው ጥቅም ባለመኖሩ በሰላማዊ መንገድ እጅ ልንሠጥ ችለናል ብለዋል።

የቡድኑ ዓላማ ህዝባዊ አለመሆኑን ጠቁመው ፤ ተበታትነው የሚገኙ ርዝራዥ የቡድኑ ታጣቂዎች የሸኔን የጥፋት ዓላማ በመገንዘብ ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።