Get Mystery Box with random crypto!

በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮ-አሜሪካ የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ ዋሽንግተን ዲ.ሲ. | Natnael Mekonnen

በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮ-አሜሪካ የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ

ዋሽንግተን ዲ.ሲ. የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ከዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ-አሜሪካ ቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን ዲሲ አካሄደ። በዚሁ ፎረም ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ገንዘብ ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያን እና አሜሪካውያን ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ባለፉት ጥቂት አመታት የተለያዩ የውጭ እና የውስጥ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ አሁንም ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸው ኢኮኖሚያችን እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ የማለፍ አቅም የፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በመንግስት እየተተገበረ ያለው መጠነ ሰፊ የሪፎርም ስራ እና በመሰረተ ልማቶች ላይ በተከናወኑ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም፣ በምግብ ራስን ከመቻል እንዲሁም ዘላቂ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ እና ከተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት አንጻር ትልቅ ድርሻ የሚይዘው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም አሜሪካውያን ባለሀብቶች አገራችን ኢትዮጵያን መጥተው እንዲጎበኙ እና ያሏትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲያዩ ግብዣቸውን አስተላልፈዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ስለሺ በቀለም በበኩላቸው አገራችን ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያላት መሆኗን እና በተለያዩ ጊዜያት የከፍተኛ ባለስልጣናት የስራ ጉብኝቶች የተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ባለፈው ዓመት በዩ.ኤስ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፎ ማድረጉን እና በወቅቱ ክቡር ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዓብይ ከአሜሪካ አስተዳደር፣ ኮንግረስ፣ እና በግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ ከተሰማሩ አካላት ጋር ውጤታማ ውይይቶች ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በዚህ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት እና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሁም ኢንቨስተሮች ሊያገኙ የሚችሉትን የተለያዩ ማበረታቻዎችን አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ ቀርቧል። በተጨማሪም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ስኬታማ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን እና የተለያዩ አሜሪካውያን የስራ ሃላፊዎችን ያካተተ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፤ በፎረሙ የተሳተፉ አሜሪካውያን ባለሀብቶች መንግስት እያካሄደ ያለው ሪፎርም በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮች መዋእለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው በቀጣይ ከኢትዮጵያውያኑ ባለሀብቶች ጋር ለሚኖራቸው ፍሬያማ ግንኙነት መሰረት የሚጥል ነው በማለት በሀገሪቱ ያሉ አማራጮችን ለማየት ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል። The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia