Get Mystery Box with random crypto!

በባህርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት ሊቦ ከምከም ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በሰላም ወደ መንግስትና ህዝብ | Natnael Mekonnen

በባህርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት ሊቦ ከምከም ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በሰላም ወደ መንግስትና ህዝብ እየተቀላቀሉ ነው።

በደቡብ ጎንደር ዞን በሊቦ ከምከም ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች የአማራነት ጥያቄ አለን በሚል ሽፋን ትጥቅ አንግበው የተነሱ ታጣቂ ሀይሎች በሰላም እጃቸውን ለወረዳው ኮማንድ ፖስት እየሰጡ ነው።

የታጣቂ ኃይሉ ሰብሳቢ እሸት አለሙና ፈንታሁን አስናቀው እንደተናገሩት የአማራ ጥያቄዎች በትጥቅ ትግል ይፈታሉ ብለን አስበን ጫካ ገብተን ነበር። ነገር ግን ሰላም በጦርነት አይመጣም፣ ከሁለቱም በኩል ያለውን አየነው ተገነዘብነው በአፈሙዝ የሚፈታ ነገር እንደሌለ ተረድተን ከህዝባችን ጎን ሆነን ብንመካከር ይሻላል ብለን ተመልሰናል ብለዋል።

በኮማንድ ፖስቱ የሰላም ጥሪ ከተላለፈ በኋላ  ዛሬ መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም የገቡትን 16 ታጣቂዎች ጨምሮ 57  ያህል ታጣቂዎች በሰላም ገብተዋል።

የሚሰጣቸውን የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰውና በምርጫቸው ከመንግስት ጎን በመሰለፍ  ሀገራቸውንና ህዝባቸውን የሚያገለገሉ መሆኑን የሊቦ ከምከም ወረዳ ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።

በስፍራው ተልዕኮ እየፈፀመ የሚገኘው ክፍለጦር ሬጅመንት አዛዥ እና የሊቦ ከምከም ወረዳና የአዲስ ዘመን ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሻለቃ ጌታ በላይነህ ሰራዊቱም ሆነ ህዝቡ ሰላም ይፈልጋል። ሰው እንዲሞት አንፈልግም ችግሮቻችን በሽምግልና፣ በንግግርና በመድረክ መፍታት እንችላለን ብላችሁ መምጣታችሁ ተገቢ ነው ብለዋል።

በጋራና በትብብር ሀገርንም ክልልንም መታደግ ይቻላል በጦርነትና በመሳሪያ አፈሙዝ የሚፈታ ችግር አለመኖሩን ተረድታችሁ በሰላም ወደ መንግስትና ህዝብ በመምጣታችሁ ለክልሉ ሰላም ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉም አሥገንዝበዋል።

ሻለቃ ጌቴ በላይነህ የቀሩ ታጣቂ ሀይሎችም ከማያዋጣ ሽፍትነት ተመልሰው ወደነበሩበት የሰላም ኑሮ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል ሲል የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዘመቻ መምሪያ የላከልን መረጃ ያመለክታል።