Get Mystery Box with random crypto!

ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ዳያስፖራ | Natnael Mekonnen

ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ዳያስፖራዉ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ፡

የትምህርት ሚኒስቴር የጀመራቸውን ሪፎርም ስራዎችና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት በውጪ ሀገር ነዋሪ የሆነው ኢትዮጵያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቀረበ ፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች ጋር በተካሄደ ውይይት ላይ የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ እንደተናገሩት በሁሉም የትምህርት ርከን እየተካሄደ ያለው ሪፎርም ለመጪው የኢትዮጵያ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

የሕወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ ምክንያት የወደሙ አጅግ በርካታ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በትምህርት ሚኒስቴር የግንባታ እቅዶች መቅረባቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሀኑ እነዚህን የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በውጪ ሀገር ነዋሪ የሆነው ዳያስፖራ ተሳታፊ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በትምህርት ስርአቱ ላይ እየታየ ያለው የጥራት ፣ የብቃትና ሁለንተናዊ ክህሎት ያለው ዜጋን ከማፍራት አንጻር ያለው ችግር ስር የሰደደ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የትምህርት ጥራትና ብቃት ላይ ስርነቀል የሆኑ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከታችኛው የትምህርት ርከን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ያለው ችግር ሀገርን ለመገንባት መሰረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ለዚህ ስኬታማነት በውጪ ሀገር ያለው ኢትዮጵያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ የከፍተኛ ትምህርት ባለሙያና ተመራማሪ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይም ሁለተኛ ትውልድ የሆነው ዳያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መሰረታዊ ችግር ባለበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ በመሳተፍና የእንግሊዝኛ ቋንቋን በማስተማር የትምህርት ስርአቱን የማስተማሪያ ቋንቋ ለመቀየር በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች ያላቸውን ትርፍ ጊዜ ጭምር በመጠቀም በከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፣ በከፍተኛ ትምህርት አመራር ፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች ፣ ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎችን የማማከርና የማስተማር ዘርፍ ላይ ቢሰማሩ ለትምህርት ሪፎርሙ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ መጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የሚገነባበት እድል ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡


በለንደን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በትምህርት ዘርፍ የተጀመረውን ሪፎርም ከግብ ለማድረስ በዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪ የሆኑ ዳያስፖራ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች በአለም አቀፍ ደረጃ በሚቋቋመው የትምህርት ባለሙያዎች የዬኬ ቻፕተር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸዉን ከኤምባሲዉ ያገኘነዉ መረጃ አመልቷል፡፡