Get Mystery Box with random crypto!

በሰሜን ጎንደር ዞን ስር ያሉ ሁሉም ያልተፈተኑና ፈተናውን ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመ | Natnael Mekonnen

በሰሜን ጎንደር ዞን ስር ያሉ ሁሉም ያልተፈተኑና ፈተናውን ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በቀጣይ አመት እንደሚፈተኑ ተገለጸ።

ተማሪዎቹ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሃገር አቀፍ ፈተናውን ያልወሰዱና ፈተናውንም ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በቀጣይ አመት በሚሰጠው ፈተና ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከክልል በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የቲቶሪያል ትምህርት በወረዳቸው ከሚገኘው አዲምህረት ትምህርት ቤት ከግንቦት ወር ጀምሮ እንደሚሰጡ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ ወ/ሮ አጸደ በሬ አሳውቀዋል።

በቀጣይ ሁለት የክረምት ወራቶች የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ የገለጹት ወ/ሮ አጸደ በሬ በተለያዩ ምክንያት ከወረዳው ውጭ የሚገኙ ተማሪዎችንና ወደ ወረዳው መሄድ የማይችሉ ተማሪዎችን የተማሪ መታወቂያ አይዲ ካርድ ይዘው በደባርቅ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት ከአዲ አርቃይ ከተማ ተማሪዎች ጋር መማር እንደሚችሉ አሳውቀዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል በነበረው ጦርነት በተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተገንዝቦ በ2013 ዓ.ም ኦንላይን ተመዝግበው ሃገር አቀፍ የ 12ኛ ክፍል ፈተና ያልወሰዱና ፈተናውን ወስደው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ከ 2014 ዓ.ም ተፈታኞች ጋር በድጋሚ ፈተናውን እንዲፈተኑ ከሃገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በጋራ መወሰናቸው የሚታወስ ነው።