Get Mystery Box with random crypto!

ጨዋና ጥብቅ የሆንሽው ውድ እህቴ ሆይ! እስቲ የተወሰኑ ነገሮችን ልምከርሽ ጆሮ ስጪኝ፡፡ ከጆሮሽ በ | Muslim Students

ጨዋና ጥብቅ የሆንሽው ውድ እህቴ ሆይ! እስቲ የተወሰኑ ነገሮችን ልምከርሽ ጆሮ ስጪኝ፡፡ ከጆሮሽ በፊት ወደ ቀልብሽ እንዲደርስ የምፈልገው መልዕክት አለኝ፡፡
:
እህቴ … በሸሪዓው የማይኖሩ፤ አላህ (ሱብሃኑታአላ) ያዘዛቸውን የማይሰሙና የማይቀበሉ ሴቶች በዝተዋልና መብዛታቸውን አይተሽ አትታለዪ፡፡ በሒጃብ ጉዳይ ችላ የሚሉ ሴቶች በርክተዋልና ከነርሱ አትሁኚ፡፡ ወንድ ጓደኛ የሚይዙ፣ በፍቅር ሥም አላስፈላጊና ሐራም ግንኙነት የመሰረቱትን አይተሽ አትሞኚ፡፡ ዓላማቸውና ወሬያቸው ሁሉ ፊልምና ቲያትር ብቻ በሆኑት እህቶች አትሳቢ፡፡
:
ይበልጥ በግልጽ እንምከርሽ … በርግጥ ፈተናዎች በዝተዋል፣ መከራዎች በግራ በቀኝ አይለዋል፡፡ እይታን የሚፈትኑ፣ መስሚያን የሚፈትኑ፣ …አንዳንዶቹ ዝሙት ምንም አይመስላቸውም፣ ሌሎች የገንዘባቸው ምንጭ ምንነት የማያሳስባቸውም፡፡ ተቆጣጣሪ እንደሌለው ሆነው እንደፈለጉትና እንደሻቸው ይኖራሉ፡፡
:
ይህ ዘመን በርግጥ ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ያሉት ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምን አሉ መሰለሽ … ‹ከኋላችሁ ትዕግስትን የሚጠይቅ ዘመን አለ፡፡ በዚያን ዘመን ውስጥ መታገስ ፍምን እንደመጨበጥ ነው፡፡ የናንተን ዓይነት ተመሳሳይ የሆነ መልካም ሥራ የሚሰራ ሰው የሃምሳ ሰው ምንዳ ያገኛል፡፡ …› ሐዲሡን ቲርሚዚ፣ አልሓኪምና ሌሎችም ዘግበውታል፡፡
:
አዎን … በመጨረሻው ዘመን የመልካም ሰሪ ሰው ምንዳው ብዙ ነው፡፡ ለምን ከተባለ በመልካም መንገድ ላይ ብዙ አጋዦች አይኖሩትምና ነው፡፡ በአመጸኞች መካከል የሚኖር ባይተዋር ብቻ ሆናል፡፡ አዎን ብቸኛ… እነርሱ ሙዚቃ ያዳመጣሉ እሷ አታዳምጥም፣ ሐራም ነገር ያያሉ እሷ አታይም፣ ቦይ ፍሬንድ ይይዛሉ እሷ አትይዝም … ሌላው ቀርቶ በድግምት እና በሺርክ ጭምር ውስጥ ይገባሉ፤ እሷ ግን ከሁሉም የራቀች ነፃ ናት፡፡
:
ሙስሊም በዘገቡት ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹ እስልምና ባይተዋር ሆኖ ተጀመረ ባይተዋር እንግዳ ሆኖ ይመጣል፡፡ ባይተዋር ሆኑት ምንኛ ታደሉ!.. › ብለዋል፡፡ አዎን ዕድለኞች ናቸው፡፡ እነዚያ ወንጀሎች በበዙበት ዘመን ጽድቅ የሚሰሩ፣ ሰዎች ሲያጠፉ የሚያስተካክሉ፣ ሌሎች ሲያምጹ የሚታዘዙ …
:
በቡኻሪ ዘገባ ደግሞ የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ‹ጌታችሁን እስከምትገናኙበት ቀን ድረስ አንድ ቀን መጥቶ ሌላ አይተካም ክፋቱ የባሰ ቀን የተተካ ቢሆን እንጂ፡፡› ብለዋል፡፡
:
አልበዛር በዘገቡት ሐዲሥ ደግሞ ሀያሉና ተከበረው አላህ ‹በሀያልነቴ እምላለሁ በባሪያዬ ላይ ሁለት ጊዜ ስጋትን አላደርግበትም፡፡ ሁለት ደህንነትንም አላደርግለትም፡፡ በምድር ላይ እያለ ከኔ ያልተጠነቀቀ እንደሆነ በመጨረሻው ዓለም ስጋት ውስጥ ነው፡፡ በምድር ላይ እያለ እኔን ከፈራና ከተጠነቀቀ ደግሞ የትንሳኤ ቀን ደህንነትን እሰጠዋለሁ፡፡› ብሏል፡፡
:
አዎን … በምድር ላይ እያለ አላህን ሲፈራና ሲያልቀው የኖረ ሰው የትንሳኤ ቀን የደህንነት ዋስትና አለው፡፡ ስጋትም ሆነ ፍራቻ የለበትም፡፡ ከአላህ ጋር በመገናኘቱ ይደሰታል፡፡ ጀነት በገባ ጊዜ እንዲህ በማለት ከባልደረቦቹ ጋር ይጠያየቃል፡፡ አላህ (ሱብሃኑታአላ)
:
‹የሚጠያየቁ ሆነውም ከፊላቸው ወደ ከፊሉ ይዞራል፡፡ ‹እኛ ፊት ቤተሰቦቻችን ውስጥ (የአላህን ቅጣት) ፈሪዎች ነበርን፡፡ አላህም በኛ ላይ ለገሰ፡፡ የመርዛም ቅጣት እሳት ቅጣትንም ጠበቀን፡፡ እኛ ከዚህ በፊት እንለምነው ነበር፡፡ እነሆ እርሱ በጎ ዋይ አዛኝ ነውና፡፡›ይላሉ፡፡›› (አጥ-ጡር ፡ 25-28) ካላቸውም መካከል ይሆናል፡፡
:
የወንጀል ባለቤት የሆነና በአላህ ሲያምጽ የኖረ፣ ሙሉ ሀሳቡንና ትኩረቱን ሆድና ወሲብ ላይ ያደረገ፣ የአላህን ቅጣት ያልፈራ፣ ለማስጠንቀቂያው ቁብ ያልሰጠ ሰው ደግሞ … በመጨረሻው ዓለም በፍራቻ ውስጥ ይኖራል፤ ድንጋጤም ይወርሰዋል፡፡

تَرَى الظَّالِمِينَ مُشْفِقِينَ مِمَّا كَسَبُوا وَهُوَ وَاقِعٌ بِهِم
‹በዳዮች ከሰሩት ሥራ የፈሩ ሆነው ታያቸዋለህ፡፡ እርሱም በነርሱ ላይ ወዳቂ ነው …› (አሽ-ሹራ ፡ 22)
:
ውድ እህቴ… ግልጽ በሆነው እውነት ላይ ነሽና በጌታሽ አላህ (ሱብሃነሁ ወተአላ) እውነተኛ መመካትን ተመኪ፡፡ በዲን ላይ ጽኑዎች ትንግርት ቢሆኑም ከነርሱ ለመሆን ጣሪ፡፡ አጥፊዎች የተበራከቱ ቢሆንም ብዛታቸውን አይተሽ አትታለዪ፡፡
:
አላህ በጥበቃው ይጠብቅሽ፡፡ በእዝነቱ ያካብብሽ፡፡ እሱን ከሚፈሩ አማኞችም ያድርግሽ፡፡ ወደሱ ጎዳና መንገድ ከሚጣሩትና ያወቁትን ከሚተገብሩትም ያድርግሽ፡፡
:
ውድ እህታችን … ምክራችንን የማትቀበዪ ብትሆኚ እንኳን ሁሌም እህታችን ነሽ፡፡ መልካም ነገር እንመኝልሻለን፡፡ በሌሊትም ሆነ በቀን አላህን ዱዓእ እናደርግልሻለን፡፡ ዘወትር አንችን ከመምከርና ከመጠበቅ ወደኋላ አንልም፡፡ ጥረታችን ውጤት እንደሚኖረው በአላህ ላይ ተስፋ አለን፡፡ ስኬት ከርሱ ዘንድ ነው፡፡
:
የአላህ ሰላም እዝነትና በረከት በናንተ ላይ ይሁን፡፡

https://t.me/Al_Islam_Media_Et

https://t.me/Al_Islam_Media_Et