Get Mystery Box with random crypto!

ጥያቄ በሉቃስ ወንጌል 'መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፡፡ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ | ምን እንጠይቅሎ?

ጥያቄ

በሉቃስ ወንጌል "መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፡፡ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል" ሉቃ 1:35 ላይ ይጸልልሻል የተባለው ""መንፈስቅዱስ በማርያም ላይ አስቀድሞ መምጣት ያስፈለገበት ምክንያት ለመጽለል ( ለመጋረድ፣ ለማጥለል) ሲሆን ቀጥሎም ከተጋረደው ወይም ከተጠለለው ማንነቷ ውስጥ የሚወለደው ክርስቶስ " ቅዱሱ" የእግዚአብሄር ልጅ እንዲሆንና እንዲባል ነው።"" በማለት እመቤታችን ኃጢአት ነበረባት በማለት ተቃዋሚ መናፍቃን ያስተምራሉ::

መልስ

ቃሉን አስተውለን ከተመለከትነው እመቤታችን "ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል" ሉቃ. 1:34 በማለት ለጠየቀችው ጥያቄ ነው መልአኩ "መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፡፡ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል" ሉቃ 1:35 በማለት የመለሰው በደል ኖሮባት ከዚያ ሊያነጻት አይደለም፡፡ ኃጢአት እንደሌለባትማ ከፍ ብሎ በሉቃ. 1:28 ላይ "ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፡፡ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት፡፡" በማለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በረከት ሳይሆን መርገም በነበረበት ዘመን ብሩክት ብሎ አመስግኗታል፡፡ ጸጋ በጎደለበት ዘመን ጸጋን የተሞላሽ በማለት ኃጢአትና መርገም ያላገኛት እንደሆነች ተናግሯል፡፡

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምስ "ከሴቶች ተለይታ ጸጋን የተመላችና ከሴቶች ተለይታ የተባረከች" ናት፡፡ ሊቃውንትም ይህን ክፍል "ያንቺማ ጽንስ መቼ እንደሌሎች ሴቶች ጽንስ ነዋ መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል ኃይለ ልዑል ወልድ ሥጋሽን ይለብሳል፡፡" በማለት ተርጉመውታል፡፡

ሁለተኛው ተቃዋሚዎች "ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ወዳንቺ ይመጣል" የሚለው ቃል ከተነገረ በኋላ ነው በማለት ይህ ግን በባህሪይው ቅዱስ የሆነ ጌታ ቅድስናን ስጋ ከለበሰ በኋላ ነው ያገኘው የሚለው የክህደት ትምህርት ነው፡፡ "በመጀመርያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፡፡ ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡" ዮሐ 1:1 በማለት ቅድመ አለም ቃል (ወልድ) እግዚአብሔር እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ቅድስናው የባህሪይው ከእመቤታችን ሲወለድ ያገኘው አልነበረም፡፡