Get Mystery Box with random crypto!

ጥያቄ 'ነገር ግን፥መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከርሱ በበላኽ ቀን ሞትን ትሞታለኽ | ምን እንጠይቅሎ?

ጥያቄ

"ነገር ግን፥መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከርሱ በበላኽ ቀን ሞትን ትሞታለኽና።" ኦሪት ዘፍጥረት 3፥17 ላይ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ዕጸ በለስን በበላኽ ቀን ትሞታለህ ብሎታል። አዳም ግን የሞተው 930 ዓመት ከኖረ በኋላ እንደሆነ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን። ታዲያ ምን ማለት ነው?

1ኛ. ሞት ማለት ከእግዚአብሔር መለየት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በላከው መልዕክቱ "በበደላችኹና በኀጢአታችኹ ሙታን ነበራችኹ በእነርሱም፥በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥" ኤፌ. 2፥1::

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንተን ከመከተሌ በፊት አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ ብሎ ለጠየቀው ሰው "ኢየሱስም፦ተከተለኝ፥ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው።" ማቴ. 8:22 ብሎታል። የሞተ ሰው የሞተን ሰው የሚቀብር ሆኖ ሳይሆን የሞቱ ያለቸው ከእግዚአብሔር የተለዩ በኃጢአት የሚኖሩ ለማለት ነው። ስለዚህም አዳም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላልፎ ኃጢአትን በማድረጉ ሞተ ተብሎ የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መለየቷ ነውና።

2ኛ. በርግጥም አዳም ዕጸ በለስን በበላበት ቀን ሞቷል። "እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺሕ ዓመት፥ሺሕ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ኾነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።" 2ኛ ጴጥ.3:8። እንደተባለው በእግዚአብሔር አንድ ቀን የሰው 1000 ዓመት ተብሎ ተነግሯል። ከ አምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ የገባለት ቃል ኪዳንም ምስጢሩ ከ 5500 ዓመት በኋላ ሰው ሆኖ እንደሚያድነው የሚናገር ነው።

ስለዚህ አዳምም ሆነ የአዳም ልጆች 1000 ዓመትን መኖር አልቻሉም። አዳም በ930 ዓመቱ ነው የሞተው። በዕድሜ ትልቁ የሚባለው ማቱሳላም 969 ዓመት ነው የኖረው። "ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ዅሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ኾነ ሞተም።" ኦሪት ዘፍጥረት 5:27:: ስለዚህ 1000 ዓመትን ሰው መኖር አልቻለም። በበላበት ቀን ሞቷል የተባለው በዚህ ይተረጎማል። በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ቀን አንድ ሺህ ዓመት ነው ተብሏልና።

" 2 በአሥራ ዘጠኝኛው ኢዮቤልዩ መጨረሻ በሰባተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት አዳም ሞተ ልጆቹም ሁሉ በተፈጠረበት ምድር ቀበሩት።

3 እርሱም ኣስቀድሞ በምድር ተቀበረ።ከሺህ ዓመትም ሰባ ዓመትን አጐደለ ይህችውም በሰማይ ጽላት እንደ አንዲት ቀን ነበረች።

4 እርሱም ኣስቀድሞ በምድር ተቀበረ።ከሺህ ዓመትም ሰባ ዓመትን አጐደለ ይህችውም በሰማይ ጽላት እንደ አንዲት ቀን ነበረች።" መጽሐፈ ኩፋሌ 6:2-4 በማለት በበላበት ቀን መሞቱን ያስረዳል።