Get Mystery Box with random crypto!

የቀጠለ... ሌላው 'ጸለለ' ለሚለው ግዕዙ በራሱ ሁለት አይነት ፍቺ (ትርጉም) አለው ጠ | ምን እንጠይቅሎ?

የቀጠለ...

ሌላው 'ጸለለ' ለሚለው ግዕዙ በራሱ ሁለት አይነት ፍቺ (ትርጉም) አለው ጠብቆና ሲላላ "ጸለለ" ላልቶ ሲነበብ "መጥለል፣ መጥራት፣ በአየር ወይም በውኃ ላይ ተዘርግቶ መሄድ... አጽለለ ደግሞ አጠራ፣አጠለለ፣አሰፈፈ ፣ አንጓለለ" ተብሎ ይፈታል፡፡ ላልቶ ሲነበብ በግዕዝ አረባብ "ጸለለ፣ ይጸልል፣ ይጽልል፣ ጸሊል ሲሆን ግሱን በቅርብ የሴት አንቀጽ ሲረባ "ጸለለኪ፣ ይ'ጸ'ልለኪ፣ይጽልልኪ..." ይሆናል፡፡ በሉቃ. 1:35 ላይ ግን የተጠቀሰው ቃል በግዕዙ "መንፈስ ቅዱስ ይመጽዕ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይ'ጼ'ልለኪ" ነው የሚለው፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ግን ቃሉ ሲላላ ያለው የአረባብ መንገድ በሉቃስ ወንጌል ላይ ያለውን "ይ'ጼ'ልለኪ" አያስገኝም፡፡

"ጸለለ" ሲጠብቅ ደግሞ ትርጓሜው "መጽለል፣ በላይ ሆኖ ማጥላት፣ ጥላ መሆን፣ ማልበስ፣ መክደን፣ መሸፈን፤ መከለል፤ መጋረድ" ተብሎ ይፈታል፡፡ ጠብቆ ሲነበብ ባለው የአረባብ መንገድ ነው በሉቃስ ወንጌል ላይ የተጻፈውን ይ'ጼ'ልለኪ የሚለውን የሚያስገኘው፡፡

ስለዚህ ጠብቆ ሲነበብ ካለው ትርጉም ጋር የሚሄድ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንም በሉቃ 1:35 ተክተን ስናነበው "የልዑል ኃይል ይጋርድሻል፣ በላይ ሆኖ ያጠላልሻል፣ ጥላ ይሆንሻል፣ ያለብስሻል፣ ይከድንሻል፣ ይሸፍንሻል፣ ይከልልሻል" የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ "ማንጓለል፣ ማጥራት፣ ማጥለል፣ የሚል ግስ እና በሁለተኛ አንቀጽ ለእመቤታችን አልተነገረም፡፡

በእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስም "The Holy Ghost Shall come up on thee, and the power of the highest shall 'overshadow' thee" luke 1:35 ገልጾታል፡፡ ይጸልልሻል የሚለውን "Overshadow" በማለት ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ይህም ቃል "To shelter, to protect " ጥላ መሆን (አስቀድሞ) መጋረድ ተብሎ ይፈታል፡፡

ስለዚህም ቃሉ በኃይለ ልዑል መጋረድ መጠበቋን ፣ መሸፈኗን ከኃጢአት መከልከሏን ነው፡፡" የሚያሳየው:: በማር. 9:7፣ ሉቃ 9:34፣ ማቴ 17:5 ላይም Overshadow የሚለው መጋረድ ወይም መከለል በሚል የተፈታ ነው፡፡ ጸለለ የሚለውም ይህን የተከተለ ነው፡፡

ዋቢ፦ ሐውልተ ስምዕ (መምህር ኃይለ ማርያም ላቀው)
- ወልታ ጽድቅ (በአማን ነጸረ)