2020-06-28 10:34:25
ክፍል ሠላሳ ስምንት
የአየር_አጋንንት_ፈተና በሱባኤ ወቅት እና በገዳማት
በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም
አጋንንት በሕይወታችን የሚያደርስብንን ችግር እስክናውቅ እንቸገራለን፣ ውጊያው እስኪገባን ግራ እንጋባለን፣ እውነቱ እስኪገለጥልን እውነቱ ሐሰት ይመስለናል፡፡
ሼር በማድረግ ለወዳጆ አዳርሱ!
ተወዳጆች ሆይ በክፍል ሠላሳ ሰባት በአጋንንት በመፈተናችን ምን ጥቅም እናገኛለን በሚል ርዕስ ተነጋግረናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ብዙዎቻችን የምንቸገርበትን እናያለን፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ግን ትንሽ ቅሬታዬን ልናገር፡፡ ሰሞኑን ተከታታይ ትምህርታችን እንደ ቀድሞ በየእለቱ እያቀረብኩላችሁ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቴ ሁለት ነበሩ፡፡ አንደኛው የምጽፈው መጽሐፍ ነበር፡፡ ሁለተኛው እንዳያችሁት በቪዲዮ ሁለት ትምህርት ለቅቄ ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ ከማንበብ እስከ መዘጋጀት ጊዜ ይፈልጋል፡፡
እንደዛም ሆኖ በተቻለኝ አቅም አቀረብኩት ብዙዎችም ተማሩበት፡፡ አንዳንዶቻችሁ ግን ለምን በቪዲዮ ሆነ፣ በጽሑፍ አድርግልኝ፤ ይህ በዩ ትዩብ የሚለቀቀውን የቪዲዮ ትምህርት ካለብን ሁኔታ አንጻር ማየት አንችልም አላችሁ፡፡ ጥሩ! ግን ሁሌም ትምህርት የሚሰጠው በጽሑፍ ብቻ ነው? እኔስ በጽሑፍ ትምህርት ብቻ ተገድቤ እንድቆም ነው የምትፈልጉት? ደግሞስ በአረብ አገራት በአውሮፓና በአሜሪካ ወዘተ በሥራጰጫና ለማንበብ የማይመቻቸው ግን እየሠሩ የሚያዳምጡ ስንቶች አሉ።
በእርግጥ ይገባኛል አብዛኞቻችሁ የምታውቁኝ በጽሑፍ ትምህርቶቼ ነው ግን ሁሌም እንደዚህ አትጠብቁ፡፡ አንዳንዶች ትምህርት ለምን በቪዲዮ ለቀክ ብለው ቅናት ይሁን ሞኝነት ባላውቅም ለሞራል የምይመጥን ኮሜንት የጻፉትን ብሎክ አድርጊያቸዋለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ጋሽ ማርቆስ የሰጠኝ መብት ስለሆነ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ እሺ ጊዜያችንን ላለማባከን ወደ ቀጣይ ትምህርታችን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወለላይቱ እመቤት ድንግል ማርያም ነገ ሰኔ 21 ቀን በጎልጎታ የሰኔ ጎልጎታ የተሰኘውን ድንቅ የቃል-ኪዳን ጸሎት ጸልያ ለእኛ ለልጆችዋ ቃል-ኪዳን የተቀበችበት ቀን ስለሆነ ነገ የእመቤታችን ወዳጅ እና ልጅ የሆናችሁ በእለተ ቀኗ የሰኔ ጎልጎታን ጸልዩ፡፡ ለምኗት፣ ተማጸኗት፣ ከዚህ ወረርሽኝ በዘርፋፋ ቀሚስሽ በክንፈ ረድኤትሽ ሰውሪኝ፣ ለዓመቱ አድርሺኝ ብላችሁ ጸልዩ፡፡ ይህ በረከት እንዳያልፋችሁ አደራ!
ወዳጆቼ አብዛኞቻችን ወደ ገዳማት ለጸሎት እንሄዳለን፡፡ በሄድንበትም ገዳም ለሰባት፣ ለዐሥራ አራት ቀናት ወይም ለወራት በጸሎት ለማሳለፍ እናቅዳለን፡፡ ገዳም እንደሄድን ከፍተኛ ያለመረጋጋት ክስተት ውስጥ ገብተን ግን ባሰብንበት ሳይሆን ባላሰብንበት ቀን ወደ ቤታችን እንመለሳለን፡፡ በሄድንበት ገዳም መረጋጋት ያቅተናል፣ ሂድ ሂድ የሚል መንፈስ ከውስጣችን ይገፋናል፡፡ ይህ እንግዲህ የአየር አጋንንቱ፣ ውስጣችን ያለው ዓይነ ጥላው፣ ዛሩ፣ ድግምት መተቱ ሰላምና ምቾት ሲያጣ እኛን መስሎ በመገፋፋት ከሄድንበት ገዳም ይመልሰናል፡፡
አንዳንዱን ሊፈወስ፣ ሊቀደስ በሄደበት ገዳም ጊዜውን በወሬና በቧልት እያሳለፈበት፣ ከገዳሙ የጸሎት ሥርዓት እያራቀው ቦታውን ያለማምደውና በዓለም ላይ የተወውን፣ ንስሐ ሊገባበት ያለውን ወይም የገባበትን ኃጢአት እዛው ገዳም ያስፈጽመዋል፡፡ የአየር አጋንንቱ በእንዲህና በሌሎችም አጋንንታዊ ጥበቦች የጀመርናትን ትንሽዋን መንፈሳዊ ሕይወት የርኩሰት እና የከንቱ ሕይወት ያደርግብናል፡፡
ይህ በሚሆንበት ጊዜ እላያችን ላይ ያለው አጋንንት ጾሙን፣ ጸበሉን ጸሎቱን ይለምድና ከነፍስ ከሥጋችን ተዋሕዶ፣ የገዳምን ሕይወት ለምዶ አብሮን ይኖራል፡፡ እኛም ‹‹እዚህ ገዳም ከተቀመጥኩ ሁለት፣ አምስት … ዓመቴ ነው›› እያልን ከመዳን ይልቅ ዓመታት ቆጣሪ፣ ለገዳሙም ሥርዓት አስቸጋሪ ሆነን በመባከን እንኖራለን፡፡ የአየር አጋንንቱ ዓላማችንን በማዘናጋት ድኅነታችንን ያዘገይብናል ያሳልፍብናል፡፡ እኛም አጋንንቱን ገዳሙን ለምደን በከንቱ እንኖራለን፡፡ ቤተሰብ ከዛሬ ነገ ይድናሉ እያሉ በባዶ ተስፋ ይኖራሉ፡፡
ሱባኤውን ብንመለከት ብዙዎቻችን እንዳቅማችን ሱባኤ እንገባለን፡፡ እንደ ፍልሰታ ያለ የሱባኤ ወቅት ሁሉም ለጾም ለጸሎትና ለሱባኤ ይነሳሳል፡፡ ግን አብዛኛው ምዕመን ጾመ ፍልሰታን በሱባኤ አያሳልፍም፡፡ የበረቱትም ዝግ ሱባኤ አልያም አርምሞ ቢይዙም የአየር አጋንንትን ስውር ጥቃት ባለማወቃቸው ሱባኤያቸው ይሰናከላል፡፡ የአየር አጋንቱ በሱባኤ ወቅት ከበድ ብሎ በመምጣት የዘጉ አባቶችን በመፈተንና ፈትኖም ከሱባኤ እስከ ማስወጣት ይደርሳል፡፡ የሚገርመው ማንኛውም ሱባኤ ገብቶ ሳይጨርስ የወጣን ሰው ብትጠይቁ ፈተናው በዝቶባቸው፣ አሟቸው፣ ከሕመማቸው ጽናት የተነሳ መጸለይ አቅቷቸው እንደወጡ አይነግሯችሁም፡፡ የአየር አጋንንቱን የፈተና ገመና ይደብቃሉ፡፡ መልስ እንዳገኙ የሚናገሩም አሉ፡፡
ሱባኤ የገባነው በጸሎት በርትተን ችግራችንን ለማስፈታት ስለሆነ ችግራችን ከእኛው ጋር በእንጥልጥል እንዲቀር የአየር አጋንንቱ ከፍተኛ ፈተና ሊያመጣብን ይችላል፡፡ በተለይ በሱባኤ ውስጥ ቁርጥማት፣ ውጋት፣ የራስ ምታት፣ ብርድ ብርድ የማለት፣ ጽኑ ረሃብና የውሃ ጥማት፣ የማናውቀው ፍርሃት ያመጣብንና እኛም ‹‹ሱባኤ ገብቼ ከምሰቃይ እንደ ሰዉ ሆኜ ብጸልይስ፣ እግዚአብሔር በጊዜው ሊሠራ እኔ ምን ላመጣ ነው›› በማለት በሕሊና ይፈትነናል፡፡ እኛም ይህንን የሐሳብ ጫና መቋቋም ሲያቅተን ለአየር አጋንንት ሐሳብ በመገዛት ከሱባኤ እንወጣለን፡፡
ሱባኤ ገብተው ፈተናውን የተቋቋሙትን ደግሞ ሌሊት በዘንዶ፣ በእባብ፣ በጅብ እና በሌሎችም እየተመሰለ እያስፈራራ ይፈትናቸዋል፡፡ አንዳንዶችን ደግሞ ትዕግሥት በማሳጣት ከሱባኤው ውጣ ውጣ በማለት እረፍትና ሰላም እየነሳቸው ያስወጣቸዋል፡፡ የአየር አጋንንት ሱባኤ ስንገባ የማያባራ የክፋት ሐሳቦችን በውስጣችን እያስገባ፣ በሱባኤያችን ግራ እንድንጋባ ያደርገናል፡፡ በዚህ ስልቱ ያለመረጋጋትን ያጠናውተንና አቋርጠን እንድንወጣ ያደርገናል፡፡
የአየር አጋንንት በሱባኤ ወቅት ድንገተኛ ማዕበል ስለሚሆንብን የሚመጡብንና የሚገጥሙን ፈተናዎች ከእሱ መሆኑን ካወቅን ሱባኤያችንን ልናቋርጥ አይገባም፡፡ በተረፈ ስለ ሱባኤ ሥርዓትና ፈተና ‹‹ከእመቤታችን በሱባኤ መልስ የምናገኝባቸው ጠቃሚ መንገዶች›› የሚለውን መጽሐፌን አንብቡ፡፡
‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል›› ት.ሆሴ 4÷6
‹‹ከትውልዱ ማን አስተዋለ?›› ት.ኢሳ 53÷8
ክፍል ሠላሳ ስምንት
የአየር አጋንንት ክፉ ቂመኛ ያደርጋል
ይቀጥላል ….
ሰኔ 20-10-12 ዓ.ም
አዲስ አበባ
@Mitinkimem
@Mitinkimem
@Mitinkimem
2.3K viewsYishak Kelemework, edited 07:34