Get Mystery Box with random crypto!

... አንተም አትኖርም! ሰዎች ከታሪካቸው ይቀዳሉና ታሪክህ ባይኖር አንተም አትኖርም፤ ያሳለፍከው | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

... አንተም አትኖርም!

ሰዎች ከታሪካቸው ይቀዳሉና ታሪክህ ባይኖር አንተም አትኖርም፤ ያሳለፍከው መጥፎም ሆነ ጥሩ ነገር ባይኖር የዛሬው አንተም ባልነበርክ ነበር። ብዙዎች ብዙ የሚያልፍ የማይመስል ስቃይን አሳልፈዋል፤ ዛሬ በዛው አስከፊ ህመም ውስጥም ያሉ ሰዎች ይኖራሉ። ነገር ግን የሁኔታው ክብደትና ፋታ መንሳት ከማለፍ አይከለክለውም። ሁሉም በጊዜው ይታለፋል፤ ታሪክ ይሆናል። ትናትህን ባታልፍ ዛሬህን ባለየህ ነበር፣ ዛሬንም ካላለፍክ ነገን ልታየው አትችልም። ዛሬ ምንም ሊገጥምህ ይችላል፣ አሁን በየትኛውም አስከፊና አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ልትሆን ትችላለህ። አንድ ነገር ግን አስታውስ:- ከዚህ ከባድ ጊዜና ሁኔታ በተሻለ ሊሰራህና ብቁ ሊያደርግህ የሚችል አጋጣሚ የለም። መከዳትን፣ መገፋትን፣ መጠላትን የሚወድ የለም፤ ባይወደውም ግን ሊያልፍበት ግድ ነው። በመንገዱም መሰራቱ የግድ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! መሆን የሚገባህን ሰው እስክትሆን መሰራት ያለበት ስራ ይሰራል። አንቺን የምትመጥንሽ ሴት እስክትፈጠር ስቃዩ ይቀጥላ፤ ለቅሶሽ አያበቃም፤ ህመምሽ አይድንም። መልቀቅ ሲገባሽ አጥብቀሽ የያዝሽው እሾህ እስክትለቂው ድረስ እጅሽን መውጋቱንና ማድማቱን አያቆምም። እሾሁን ይዘሽ ለህመምሽ ሌላ ተወቃሽ አትፈልጊ። ድህነትሽ በእጅሽ እንደሆነ አስተውይ። ነገር ግን እርሱም ቢሆን በበቂ ሁኔታ ካላስተማረሽና ብቁ ካላደረገሽ በፍፁም አይተውሽም። ተዓምር የሚመስል ታሪክ አሳልፈሽ ተራ ህይወት አትኖሪም፤ ከባዱን ትናንት አልፈሽ መደበኛ ህይወት አትኖሪም። የጣለሽ መሰናክል የውድቀትን ህመምና ዳግም የመነሳትን ክብደት በሚገባ ያስተምርሻል፤ መከዳትሽ፣ በሌላ መተካትሽ የሰዎችን ለስሜታቸው መገዛትን ያስገነዝብሻል። ታሪክሽም ሆነ አሁንሽ አስተማሪ ነውና የተሻለችውን አንቺ ፍጠሪበት።

አዎ! ትናንትህ፣ የቀደመ ታሪክህ፣ ያለፈ ስቃይና ብሶትህ ባይኖሩ አንተም አትኖርም። አንተ ማነህ? የሚጨበጥ የሚዳሰሰው፣ አይን አፍንጫ አፍ እግር እጅ ያለው አካልህ አይደለህም። አንተ መንፈስህን ነህ፤ ስሜትህን ነህ፤ ማንነትህን ነህ፤ ስብዕናህን ነው። አካልህ ቢገድብ አስተሳሰብህ አይገደብም፤ ሰውነትህ ቢታሰር አዕምሮህ አይታሰርም፤ እጅ እግርህ ቢጎዳ ማመዛዘን አታቆምም። ይህን ገደብ አልባው ማንነት ደግሞ አንተ ነህ። በታሪኮችህ ተሰርተሃል፤ በውጣውረዶችህ ተገንብተሃል፤ በከፈልከው ዋጋ ለዚህ በቅተሃል። አሁን ከሁለት አንዱ ሰው መሆንህ አይቀርም። አንድ ታሪክህ የሰራህ፣ ሁለት ታሪክ እየተሰራብህ ያለህ። ሁለቱም በጊዜያቸው እጅጉን በጣም አስተማሪና የሚያንፁ ናቸው። ታሪክህ ቢሰራህ ዳግም የቀድሞ ስህተትና ስቃይ ውስጥ የመግባት እድልህ ይቀንሳል፤ ታሪክ ቢሰራብህ አዲስ ማንነት እየተሰራ እንደሆነ አስበህ ሁኔታዎቹን አምነህ መቀበልና ከእነርሱ መማር ይኖርብሃል።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q