Get Mystery Box with random crypto!

ልቤን መልስልኝ! ፍቅር ነህ ፤ አባት ነህ ፤ ደግ ፣ አዘኛ ፣ አሳቢ ንፁህ ጌታ ፣ ፍፁም አ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ልቤን መልስልኝ!

ፍቅር ነህ ፤ አባት ነህ ፤ ደግ ፣ አዘኛ ፣ አሳቢ ንፁህ ጌታ ፣ ፍፁም አምላክ ነህ ። ለስራህ የሚመጥን ቃል ባይኖርም ፣ የሚገልፅህ አገላለፅ ባይገኝም አንተ ግን የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ ነህ ። ትናንት ነበርክ ፣ ዛሬም አለህ ፣ ነገም ለዘለዓለም ትኖራለህ ። ይቅርታህ እጅግ ግሩም ነው ፤ ሳትለመን የምትምር ፣ ሳትጠየቅ የምትፈውስ ፣ ሳይማፀኑህ ፣ ሳያለቅሱብህ ይቅር የምትል ፣ ትዕግስትህ ገደብ የሌለው ፣ ጠብቀህ የማይደክምህ ፣ ለቅንነትህ ዳርቻ ፣ ለቸርነትህ መጨረሻ የሌለህ አንተ በእርግጥም ፍቅር ነህ ፣ አባት ነህ ፣ ቸር ጠባቂ ነህ ። ስትምር ልኩን ታውቀዋለህ ፣ ይቅር ስትል ማሳረፉን ትችላለህ ። ቃል አለህ በሰማይ በምድር ልጆችህን ደጋግመህ ለመማር፣ ይቅር ለማለት ፣ ለማስተማር ። ቃልህንም ስትጠብቅ ኖረሃል ፣ ከአባትም በላይ አባት ሆነህ በቃልህ ልክ ተገልጠሃል ፤ ምህረትህንም ያለገደብ ሰጥተሃል ።

አዎ! ጀግናዬ..! የሚመጥነው ቃል ብታጣ ፣ የሚወክለው አገላለፅ ባታገኝ ፍቅር ነህ ፣ ደግ ፍፁም አምላክ ነህ በለው ። ነገር ግን ፍቅሩ እስኬት ይሆን ? ከፈጣሪ ውጪ ምህረትን ማን ያውቃል ? ይቅርታን ማን ይወክላል ? በንፅህና ማን ይገለፃል ? በትዕግስት ማን ይወከላል ? ምህረቱ እንጂ ስራችን መቼም ከፊቱ አያቆመንም ፤ ቸርነቱ እንጂ ምግባራችን ስሙን ለመጥራት አያበቃንም ፤ ርህራሔው እንጂ ማንነታችን ከቤቱ አያቀርበንም ። እለት እለት ብንበድልም እለት እለት እየማረ እዚህ አደረሰን ፤ በየቀኑ ብናሳዝነው እስከዛሬ ታገሰን ፤ ሳናቋርጥ ብናስቀይመው ፣ ከትዕዛዙ ብንወጣ ፣ ከመንገዱ ብንለየ ጥበቃው ግን ሁሌም አብሮን ነው ። ልጅ በአባቱ ይመካል ፤ በእናቱም ይፅናናል ። አባትነቱ በፈጣሪነት ውስጥ ነውና ክብርን ክብር ላይ እየጨመረ እዚህ አድርሶናል ፤ ለዚህም አብቅቶናል ።

አዎ! በእርግጥም አምላክን ምን ይገልፀው ይሆን ? ፍቅር ነው መባሉ የፍቅርን ዋጋ ከማግዘፉ በላይ እርሱን አይወክለውም ፤ ፍፁም መባሉም የፍፁምነትን ዳርቻ ቢያሳይ እንጂ ብቻውን ሊገልፀው አይችልም ። መምከር ፣ ማስተማር ፣ መገሰፅ ሲያውቅበት ፣ በምህረቱ ብዛት እያስነባ ፣ በማያልቀው ይቅርታው እያስለቀሰ ፣ በማይገደበው ቸርነቱ ልብን እየሰረሰረ ዘልዓለማዊ ትምህርትን ያስተምራል ፤ እንከን አልባውን ምክር ይለግሳል፤ በቃሉ ብቻ ሰላምን ያድላል ፣ ፍቅርን ይሰጣል ፤ ፈውስን ይቸራል ። አውቀህ የምትጨርሰው ሳይሆን የሚውቅህ አምላክ አለህ ። እውቀቱም ፍፁም ነውና ሳትነግረው የሚያስፈልግህን ያውቀል ፤ ለዛም ከሌላው የተለየ መንገድን ሰጠህ ፣ በሚመጥንህ ልክ አጠነከረህ ፣ አስተማረህ ፣ ደገፈህ ። ምህረቱን እያሰብክ ቀና በል ፤ በይቅርታው ዳግም አንሰራራ ፤ በቸርነቱ በሚገባ ተማር ። "የማያልቀው በደሌን ፍፃሜ በሌለው ምህረትህ ሸፍንልኝ ፤ ዳግም እንዳልበድል ልቤንም መልስልኝ" በለው ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q