Get Mystery Box with random crypto!

አምላክህ ማነው? ሁሉም ሰው እንደ አቅሙ ንብረት አለው ፣ ሀብት አለው ፣ ስም አለው ፣ ዝና | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

አምላክህ ማነው?

ሁሉም ሰው እንደ አቅሙ ንብረት አለው ፣ ሀብት አለው ፣ ስም አለው ፣ ዝና አለው ፣ ታሪክ አለው ፣ ዘር አለው ፣ ብሔር አለው ። ከዚህ ሁሉ አምላኩ ፣ ገዢውና ጌታው የሆነ ፣ ከመዓቱ የሚያድነው ፣ ከህመሙ የሚፈውሰው ፣ ከለምፁ የሚያነፃው ፣ ከችግሩ የሚያወጣው ፣ ነፍሱን የሚያሳርፍለት ፣ መረጋጋትን የሚድለው ከፈጣሪው ውጪ አንዳች ነገር የለም ። በምድራዊ ህይወትህ ብዙ የሚያስመካህ ነገር ሊኖርህ ይችላል አምላክን እንደ አምላክ ካለስቀደምክና ካልተደገፍከው ግን ወዳቂ ነህ ። ማንም ምንም ከምድር መፈጠር በፊት ከነበረ ፣ ከምድር ማለፍ ቦሃላም ከሚኖር ዘላለማዊ ህያው አምላክ የሚበልጥ ነገር የለም ። ብታከብረው ትከበራለህ ፤ በስሙ ብትነግድ ፣ ሽፋን አድርገሀው ብትበድል ፣ የግል አቋምህን ብታራምድ ፣ ጥላቻህን ብታሳብቅ ከሁሉ ቀድመህ የምትጠፋው አንተ ነህ ። ሁሉንቻይ ፈጣሪ ሁሉን ይችላል ፤ ሲቆጣ ግን ሁሉ ነገርህን ያጠፋዋል ።

አዎ! ጀግናዬ..! አምላክህ ማነው ? ህያው የአለም ፈጣሪ ቅዱስ እግዚአብሔር (አላህ) ወይስ ምድራዊ ታፔላና ስም ? አልፋና ኦሜጋ ቸር አምላክ ወይስ ዘር ፣ ቋንቋና ብሔርህ ? ሩህሩህ ጌታ ወይስ ምድራዊ ንብረት ፣ ዝናና ስልጣን? የምታመልከውን እወቀው ፣ ከልብህ ምረጥ ። ግልፅና ግልፅ እውነታ አለ ከእምነት ውጪ ሌላው ትርፍ ነው ፤ ምድር ላይ የሚቀር ፣ ጥለሀው የምትሔደው ፣ ነገ ሌላው የሚረከበው ፣ ስምህን እንኳን የማያስታውስ ነው ። ህያው የሚያደርግህ አምላክ አለህ ፤ የሚፈውስህ ፅኑ ቃል አለህ ፤ የምትድንበት ፣ በቀኙ የሚያቆምህ ፣ የፅድቅን በር የሚከፍትልህ ብርቱ ምግባር አለህ ። ህግጋት ይገዙሃል ፤ ህሊናህ ግን ይሰራሃል ። ውስጥህ የሚመላለስ የማስተዋል ፀጋ የህይወትህ መሪ ነው ። በስሜት ሳይሆን በእውቀት ፣ በጥበብ ፣ በማስተዋል ተመራ ። ምንም ነገር አብልጠህ ልትወድ ትችላለህ ከምታምነው አምላክ የሚበልጥ ነገር ግን ሊኖርህ አይችልም ።

አዎ! ጥያቄ ይኖርሃል ፤ ልብህ ያልረካበት ጉዳይ ይኖራል ፤ ሰላም የማይሰጥህ አጀንድ አለ ። ነገር ግን ለሁሉም ጥያቄና ውግዘት የእራሱ አግባብና ስረዓት አለው ። በስረዓት አልበኝነት ገመድ ተጠልፈህ እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ ፤ በጎጠኝነት አባዜ እምነትህን እንዳትረሳ ፤ ስልጣንህን ተማምነህ ፣ በወገንህ ተመክተህ እራስህን እንዳታጣ ። ከምታነግሰው ፈጣሪ ውጪ ሌላ የምትተክለው እሾህ በውስጥህ እንዳይኖር ። ሁሉም ነገር ከእምነትህ ቦሃላ የሚመጣ ነው ፤ ፈጣሪህን አስቀድሞ የሚከተል ነው ። የትኛውም አማኝ ምግባር አለው ፤ ስረዓት አለው ፤ ህግ አለው ፤ ሀይማኖታዊ አቋም አለው ። አምላክህን በጥበብ ምረጥ ፤ በማስተዋል እወቀው ፤ ለእርሱም በሙሉ ልብህ ተገዛ ፤ ስልጣኑን ተቀበል ፤ ህግጋቱን አክብር ፤ ማንነትህንም አስገዛለት ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q