Get Mystery Box with random crypto!

በፅናት ተሻገር! በህይወት መኖር የማስደሰቱንም ያህል በእጅጉ መፈተኑ ፣ ማሳመሙ ፣ ማሳዘኑ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

በፅናት ተሻገር!

በህይወት መኖር የማስደሰቱንም ያህል በእጅጉ መፈተኑ ፣ ማሳመሙ ፣ ማሳዘኑ ፣ ማስለቀሱም የማይቀር ጉዳይ ነው ። ነገር ግን በድልም ሆነ በሽንፈት ፣ በብርታትም ሆነ በድካም ፣ እንዲሁ በጥንካሬም ሆነ አቅም በማጣት ወቅት ፅናት ያስፈልግሃል ። ብርቱ ነኝ ፣ አቅሙ አለኝ ፣ የሚችለኝ የለም ብለህ አቅምህን በደካማው ላይ ለማሳየት አትሞክር ። ጊዜው ከፍቷል ፤ መከራ በዝቶብኛል ፤ አቅም አንሶኛል ፤ ጫናው በርትቶብኛል ብለህም ተስፋ አትቁረጥ ፣ አንገትህን አትድፋ ፣ በብዙም አትከፋ ። ዋጋህ በሰው ፊት አይደለም ፤ ድርሻህ ምድራዊ አይደለም ። ስጋህ ብዙ ይመኛል ፣ ብዙ ያስባል ፣ ብዙ ይናፍቃል ለዛም በቶሎ ይሰበራል ፤ በፍጥነት ይደክማል ፤ ይዝላልም ። ስጋህ ሲደክም ፣ ተስፋ ሲያጣ ፣ ብርታት ሲጎድለው ህያዊት ነፍስህን አድምጥ ፤ የአባቷን ቃል ስማ ፤ የአምላኳን ፍቃድ ጠይቅ ። ፅናት ካለህ ሁሉን እንደ አመጣጡ ማሳለፍ ትችላለህና ምንም አይመጣብህ ፤ ምንም አይደርስብህም ፤ አንዳች አትሆንም ፤ ምንም አይነካህም ፤ አትፍራ ።

አዎ! ጀግናዬ..! በፅናት ተሻገር! በእርግጥ የሚፈትን ጊዜ ሁለመናህን ይፈትናል ። እምነትህን ፣ ፅናትህን ፣ ድፍረትህን ፣ ተነሳሽነትህን ፣ ቆራጥነትህን ፣ ታታሪነትህን ፣ ትጋትህን ፣ መልካምነትህን ፣ አርዓያነትህን በሙሉ ይፈተናል ። እያንዳንዱ ነገር እንደሚወራው ቀላል አይደለም ፤ እንደሚሰማውም ከባድ አይደለም ። ብርቱ ፅናት በመከራ ጊዜ ይፈተናል ፤ በእምነት እስከ ጥግ መፋለም በችግር ጊዜ ይፈትናል ፤ ላመኑበት ወደፊት መጓዝ በአጣብቂኝ ሰዓት ይለካል ። ፅናትን ይዘህ አታፍርም ፤ ፍቅርን አንግበህ አትሸነፍም ፤ ተስፋ ኖሮህ ወደኋላ አትመለስም ፤ በእምነት ቆመህ አትሰበርም ። ምንም የሚያስፈራና የሚያስጨንቅ ፣ የማትወጣውና የማያልፍ ቢመስልህም ሁሉም በጊዜው ያልፋል ። ምንም ነገር በምክንያት ይሆናል ፤ ማንም ቢሆን እንደ ስራው ይከፈለው ዘንድ የግድ ነው ። ያንተ አብዝቶ መጨነቅና መስጋት የሚያመጣው ነገር አይኖርም ።

አዎ! በቻልከው አቅም ላመንክበት ነገር በፅናት ታገል ፤ ለማንም ሳይሆን ለእራስህ ታመን ፤ ለአምላክህ ተገዛ ፤ በህግጋቱ ኑር ። ሰዎች ምድራዊ ህግጋትን ያወጣሉ ፤ ስረዓት ያበጃሉ ፣ ህግና ደንብን ይዘረጋሉ ። ነገር ግን እራሳቸው አፍራሹና አጥፊው ሆነው ይገኛሉ ። የማይገዛቸውን ህግ እንደ ጌታ ያዩታል ። ከህጎች በላይ የህሊና ህግ አለ፣ ነገ የሚፈርድብህ የገዛ ህገ ልቦና አለ ። ሁሉም ሲያልፍ ጥለሀው ለምትሔደው ምድራዊ ቁስ ክብርህን አታሳንስ ፤ ማንነትህን አታዋርድ ። ሌላው ይቅርና የተሸከምከው ስጋ እንኳን ባዳ ነው ። ነገ ጥሎህ ይጠፋል ። ከማንም ብትቀማ ለጊዜው ያንተ ቢሆን እንጂ ዘላለም የእራስህ የምታደርገው ነገር የለም ። ቦሃላ እንደ ጤዛ ለሚጠፋ ንብረት ፣ ዝና ፣ እውቅናና አድናቆት ብለህ ሰውነትህን አትጣ ። ዛሬ የተከተለህ ሁሉ ነገ እንደማይሸጥህ ምንም ዋስትና የለህም ። አተህም አግኝተህም ፅና ፤ ተደንቀህም ተዋርደህም ፅና ፤ ተገፍተህም ተወደህም ፅና ። ክፉውንም ደጉንም በፅናት ተሻገር ፤ አላፊውንም እንደ ሁኔታው አሳልፍ ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q