Get Mystery Box with random crypto!

የከፍተኛ ትምህርትን ሳይማሩ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት የሚሆኑትን ለመከላከል የሚያስችለው | የትምህርት ሚኒስቴር

የከፍተኛ ትምህርትን ሳይማሩ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት የሚሆኑትን ለመከላከል የሚያስችለውን ዘመናዊ አሰራር ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ተናገረ፡፡

ሰኔ 14፣2011(ሸገር 102.1)
በከፍተኛ ትምህርት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስቆም ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ የተነገረለት አዲስ የቴክኖሎጂ አሰራር ከፊታችን ሐምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ኤጀንሲው እንደሚናገረው ከሆነ ዘመናዊው አሰራር በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈፀሙ ያልተገቡ አሰራሮችንም ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡

በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ተባባሪነት የተዘጋጀው የአሰራር ሥርዓት የተማሪዎችን ሙሉ መረጃ በመያዝ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ይከላከላል ተብሏል፡፡

ከአሁን ቀደም የትምህርት ተቋማት የእውቅና ፈቃድ ለማውጣት ወይንም ለማሳደስ በቋሚነት ያልቀጠሯቸውን መምህራንን የቀጠሩ በማስመሰል መረጃ ያቀርቡ ነበር ተብሏል፡፡

ይህ ደግሞ ግለሰቦች የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን ለተለያዩ ተቋማት እያከራዩ በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱ ተነግሯል፡፡

ከአሁን ወዲህ ግን እንዲህ ዓይነት የተዘረከረኩ አሰራሮች እንደማይኖሩ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሰምተናል፡፡

ባለፉት አመታት በመስሪያ ቤቱ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ሕገ-ወጥ ተቋማትን የተመለከቱ ቅሬታዎች ከዜጎች ሲቀርቡ ነበር ተብሏል፡፡

የኤጀንሲው የስራ ሀላፊዎችም ከቀረቡት ቅሬታዎች በመነሳት ባካሄዱት ፍተሻ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሰራር ውስጥ በርካታ እና ውስብስብ ህገ ወጥነቶችን መለየታቸው ነው የተነገረው፡፡

ኤጀንሲው በሐምሌ ወር እጀምረዋለሁ ያለው የዘመናዊ አሰራር እነዚህን ችግሮች ይከላከልልኛል የሚል እምነቱን አሳድሮበታል፡፡
@MINISTERY_OF_EDUCATION