Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ_20 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰኔ ሃያ በዚች ቀን በኬልቄዶ | መዝሙረ ዳዊት

ሰኔ_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሃያ በዚች ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር #የእመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተወደደ ልጅዋ እጅ የታነፀችበት ነው፣ ከገልገላ አውራጃ አለሙት ከምትባል ቦታ የሆነው የሳፋጥ ልጅ #ታላቁ_ነቢይ_ኤልሳዕ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም (ህንጸተ ቤተክርስቲያን)

ሰኔ ሃያ በዚች ቀን በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያለ ዕንጨት ያለ ጭቃና ውኃ በሦስት ደንጊያዎች በተወደደ ልጅዋ እጅ የታነፀችበት ነው።

ይኽም በዓል ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው። ‹‹ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን›› ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በሰኔ 20 ቀን ነው። አናጺውም እራሱ ባለቤቱ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። እመቤታችን ካረገች በ4ኛ ዓመት ጳውሎስና ባርናባስ በፊሊጲስዮስ ገብተው አስተምረው ሕዝቡን አሳምነው ካጠመቁ በኋላ ‹‹እንግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሂዱ›› አሏቸው። አሕዛብ የነበሩትና አምነው የተጠመቁትም ‹‹የለመድነውን ከከለከላችሁን መካነ ጸሎት ስጡን›› አሏቸው። የከበሩ ሐዋርያትም ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልእክት ላኩባቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስም ‹‹ያለ ጌታችን ፈቃድ አንዳች ልታደርጉ አይገባምና ጸልዩ እኛም እንጸልያለን›› ብለው መለሱላቸው። ሁሉም ሱባኤ ይዘው በጸሎት ተጉ። ጸሎትና ሱባኤያቸውን ከጨረሱ በኋላ ጌታችን በሞት ያረፉትን አስነሥቶ በሕይወት ያሉትንም ደቀመዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው። ጌታችን በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች። ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጌታዬ ለምን ሰበሰብከን?›› ብሎ ጠየቀ። ጌታችንም ‹‹በእናቴ ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ነው›› አለው። ይህንን ብሎ ወደ ምሥራቅ ወሰዳቸው። በዚያም ተራርቀው የነበሩ 3 ደንጊያዎች ነበሩ። ጌታችንም ሦስቱን ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቦ አንሥቶ ጎተታቸው። ድንጋዮቹም እንደ ሰም ተለጠጡ፣ እንደ ግድግዳም ሆኑ። ቁመቱን ወርዱን መጥኖ ለሐዋርያቱ ሠጣቸው። እነርሱም እሳት እንዳየው ሰም ከእጃቸው እየለመለሙ (እየተሳቡ) ቁመቱን 24 ወርዱን 12 ክንድ አድርገው ሠርተውታል።

ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ አድርጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ። ከዚህም በኋላ ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹እንግዲህ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ›› ብሏቸው ዐረገ። ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴን ሦስትነት ወደ አንድ ሆነው አንድ ሕንፃ መታጹ የሥላሴን አንድነት ያስረዳል። በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ ለኛ ለክርስቲያኖች እጅግ ታላቅ በዓልና ደስታ ነው። ስለዚች ቤተ ክርስቲያን አባቶች ደማቸውን አፍሰውላታል፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተውላታል፣ አጥንታቸውን ከስክሰውላታል፣ ቆዳቸው ተገፏል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በአውሬ ተበልተዋል። ቤተ ክርስቲያን ግድግዳዋ ውኃ መሠረቷ ደም ነው። የማትታደስ ነገር ግን ከኃጢአት ከበደል የሚታደሱባት ርትዕት ናት። ይህች ቤተ ክርስቲያን ‹‹የክርስቶስ አካሉና ሙላቱ ናት።›› ኤፌ 1፡13፣ ቆላይ 1፡18፣14። እናም የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጣስና ትምህርቷን መቆነጻጸል የክርስቶስን አካል ማድማት ነው።

ዳግመኛም በማግሥቱ ሰኔ 21 ቀን ጌታችን ድንግል እናቱን እመቤታችንንና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ወረደ። እመቤታችንን መንበር፣ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቁርቧቸዋልና ፍጹም ደስታም ሆነ።

ዳግመኛም ጴጥሮስን እጁን ጭኖ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል። በዚህም ጊዜ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ሐዋርያት አንድ ሆነው አመስግነዋል። ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ከጌታችን እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የእነ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ፣ የአይሁድ ምኩራብ፣ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ሥርዓት መፈጸሚያ አልነበረም። እንኪያስ ‹‹ሐዋርያት የት ነበር ሕዝቡን የሚያጠምቁትና የሚያቆርቡት?›› ከተባለ እንደ ማርቆስ እናት ቤታቸውን ለሐዋርያት በሰጡ ‹‹በየአማኞቹ ቤት›› ይከናወን ነበር።

ሰኔ 20 ቀን ህንጸተ ቤተክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መታነጽ) ታላቅ በዓል ነው። ቤተ ክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሻሽ የመጣችና ሩቅ ብእሲ የመሠረታት ሳትሆን እራሱ ጌታችን አምላካችን በገዛ ደሙ የመሠረታት ናት። ሐዋ 20፡28። በዕለተ ዐርብ በዕፀ መስቀል ላይ ከጌታችን የፈሰሰው ቅዱስ ደም ቅዱሳን መላእክት በብርሃን ፅዋ ቀድተው በዓለም ሁሉ ረጭተውታል። ስለሆነም የጌታችን ወርቀ ደም በነጠበባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይሠራባቸዋል።

✞ ነብዩ_ኤልሳዕ ✞

በዚህችም ዕለት ከገልገላ አውራጃ አለሙት ከምትባል ቦታ የሆነው የሳፋጥ ልጅ ታላቁ ነቢይ ኤልሳዕ አረፈ። የዚህም ነቢይ መጠራቱ እንዲህ ኾነ ኤልያስ አልፎ ሲሔድ የሳፋጥ ልጅ ኤልሳዕን በፊቱ ዐሥራ ሁለት ጥምድ አስጠምዶ ሲያሳርስ አገኘው እርሱም በነዚያ የተሾመ ነበር ኤልያስም ሔዶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት።

ኤልሳዕም ጥማዱን ትቶ ኤልያስን ተከተለው ኤልሳዕም አባቴ እወድሃለሁ አንተንም እከተላሉሁ አለው ኤልያስም ብላቴናዬ አድርጌሃለሁና ተመለስ አለው። እርሱም ኤልያስን ከመከተል ተመለሰ ዐሥራ ሁለቱንም ጥምድ በሬዎች ወስዶ አረደ በላመ ፈጅ ጋኖችም ቀቅሎ ለሕዝቡ አቀረበላቸው እነርሱም በሉ ኤልያስንም ተከትሎት ሔደ ብላቴናውም ሆነ።

ብዙ ዘመናትም ሲያገለግለው ኖረ። ኤልያስም በሚያርግበት ጊዜ ኤልሳዕን ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ሳልወጣ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምነኝ አለው ኤልሳዕም በአንተ ያደረ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ሆኖ ይደርብኝ አለው።

ኤልያስም ኤልሳዕን ድንቅ ነገርን ለመንከኝ ነገር ግን ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወጣ ብታየኝ ይደርብህ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወጣ ባታየኝ ግን አይሆንልህም አለው።

ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሔዱ የእሳት ፈረስና የእሳት ሠረገላ መጣ ወደ መካከላቸውም ገብቶ አራራቃቸው ኤልያስም በመነዋወጥና በጥቅል ነፋስ እንደዚህ ወደ ሰማይ ዐረገ። ኤልሳዕም አይቶ የእስራኤል ኃይላቸውና ጽንዓታቸው አባ አባ ብሎ ጮኸ። ከዚህ በኋላም ዳግመኛ አላየውም ልብሶቹንም ከሁለት አድርጎ ከፈላቸው። ኤልያስም ለኤልሳዕ መጠምጠሚያውን ጣለለት በኤልሳዕ ራስ ላይም ወረደ ኤልሳዕም ተመልሶ በዮርዳኖስ ባሕር ዳር ቆመ። በራሱ ላይ የወረደች የኤልያስንም መጠምጠሚያ ይዞ ውኃውን መታባት ውኃውም አልተከፈለም የኤልያስ ፈጣሪ ወዴት ነው ይህስ እንዴት ነው አለ ከዚህ በኋላም ውኃውን መታው ውኃውም ተከፍሎ ወዲያና ወዲህ ቆመ ኤልሳዕም ተሻገረ።

በዚህም ኤልሳዕ የመንፈስ ቅዱስን ሀብት በዕጥፍ እንደተቀበለ ታወቀ። ኤልያስ የወንዙን ውኃ እንድ ጊዜ ከፈለ። ኤልሳዕ ግን ሁለት ጊዜ ከፈለ ኤልያስ አንድ ምውት አስነሣ ኤልሳዕ ግን ሁለት ምውት አስነሣ።

@mezmurochh