Get Mystery Box with random crypto!

ከዚህም በኋላ ሒዶ ወደ ኢያሪኮ ገባ የዚያች አገር ሰዎችም ጌታችን እነሆ እንደምታያት የዚች አገር | መዝሙረ ዳዊት

ከዚህም በኋላ ሒዶ ወደ ኢያሪኮ ገባ የዚያች አገር ሰዎችም ጌታችን እነሆ እንደምታያት የዚች አገር ኑሮዋ ያማረ ነው የአገሩ ውኃ ግን ክፉ ነው ሴቶች ሲጠጡት ይመክናሉ አሉት ኤልሳዕም ጨው ጨምራችሁ አዲስ ሸክላ አምጡልኝ አላቸው እነርሱም አመጡለት። ኤልሳዕም ወደ ውኃው ምንጭ ሒዶ ያንን ጨው በውኃው ምንጭ ጨመረው እንዲህም አላቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እርሱን ከመጠጣት የተነሣ የሚሞት እንዳይኖር የሚመክንም እንዳይኖር ይህን ውኃ አጣፈጥሁት። ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ኤልሳዕ እንደተናገረ ያ ውኃ ጣፋጭ ሆነ።

ከዚያም አገር ወደ ቤተል ወጣ ሲወጣም ከከተማው ሲወጡ ታናናሽ ልጆችን በጎዳና አገኘ እነርሱም አንተ ራሰ በራ ውጣ ውጣ እያሉ ይዘባበቱበት ጀመር። ወደ ኋላው ተመልሶ በአያቸውም ጊዜ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ረገማቸው የዚያን ጊዜ ሁለት ድቦች ከዱር ወጥተው ከእነርሱ አርባ ሁለት ልጆችን ገደሉ።

ከነቢያት ልጆች አንዲት ሴት ነበረች ወደ ኤልሳዕም ጮኸች ባሪያህ ባሌ ሞተ ባሌ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ ባለዕዳ ሁለቱን ልጆቼን ወስዶ ይገዛቸው ዘንድ መጣ አለችው። ኤልሳዕም አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ በቤትሽስ ምን አለሽ አላት ዘይት ካለበት ማሰሮ በቀር ለእኔ ለባሪያህ ምንም የለኝም አለችው።

ሔደሽ ከጎረቤትሽ ሁሉ የሸክላ ዕቃና ባዶ ዕቃዎችን ተዋሺ አታሳንሺ። ወደ ቤትሽም ገብተሽ በአንቺና በልጆችሽ ላይ ደጁን ዝጊ በዚያ በሸክላ ዕቃም ዘይቱን ገልብጪው የመላውንም አንሥተሽ አኑሪው አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ገብታ በልጆቿና በእሷ ደጃፏን ዘጋች እነርሱ ያቀርቡላት ነበር እርሷም እየቀዳች ትገለብጥ ነበር። ከዚህ በኋላ ልጆቿን ዳግመኛ የሸክላ ዕቃ አቅርቡልኝ አለቻቸው የሸክላ ዕቃ ሁሉ አለቀ የለም አሏት ከዚህ በኋላ ያም ዘይት ተገታ።

እርሷም ሒዳ ለእግዚአብሔር ነቢይ ነገረችው አልሳዕም ሒጂ ይህን ዘይት ሸጠሽ ዕዳሽን ክፈዪ የቀረውን ዘይት ግን የልጆችሽን ሰውነትና ያንቺን ሰውነት አድኚበት አላት።

ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ በአንዲቱ ቀን ወደ ሱማን ሔደ በዚያም አገር አንዲት ታላቅ ሴት ነበረች ወደዚያ ከመሔድ ውሎ አድሮ ነበርና እህል ይበላ ዘንድ አቆመችው። ያቺም ሴት ባሏን እነሆ ይህ የእግዚአብሔር ነቢይ ቅዱስ ነው ዘወትር በእኛ ዘንድ እያለፈ ይሔዳል። ትንሽ እልፍኝ እንሥራለት አልጋም እንዘርጋለት መብራት የሚበራበት መቅረዝንና ወንበርን ጠረጴዛንም እናዘጋጅለት ወደ እኛም በመጣ ጊዜ በዚያ ይደር አለችው።

ከዚህም በኋላ በአንዲቱ ቀን ወደዚያ ገብቶ በእልፍኙ አደረ። ደቀ መዝሙሩ ግያዝንም ያቺን የሱማን ሴት ጥራት አለውና ጠራት እርሷም መጥታ በኤልሳዕ ፊት ቆመች። እነሆ ይህን ሁሉ ክብር አከበርሽኝ ምን ላድርግልሽ ከንጉሥ ዘንድ ከአለቃም ዘንድ ቢሆን ጉዳይ እንዳለሽ ንገሪኝ በላት አለው እርሷም እኔስ በወገኖቼ መካከል እኖራለሁ አለችው። ምን ላድርግላት አለ ደቀ መዝሙሩ ግያዝም ልጅ የላትም ባሏም ሽማግሌ ነውና የሚታዘንላት ሴት ናት አለው። ደግሞ ጥራት አለው በጠራትም ጊዜ መጥታ በደጃፍ ቆመች። ኤልሳዕም የዛሬ ዓመት እንደዛሬ ልጅ ትወልጃለሽ አላት እኔን አገልጋይህን ጌታዬ አታሰቅቀኝ አለችው።

ከዚህም በኋላ ያቺ ሴት ፀንሳ ኤልሳዕ በነገራት ቀን በዓመቱ ወንድ ልጅን ወለደች። ያም ልጅ አድጎ ከአባቱ ጋራ ወደ አዝመራው መጣ። አባቱን ራሴን ራሴን አለው የሕፃኑም አባት ብላቴናውን ወደ እናቱ አስገባው አለው። ብላቴናውም ያንን ልጅ ወደ እናቱ አስገባው እናቱም እስከ ቀትር በጉልበቷ ላይ አስተኛችው።

ከዚህም በኋላ በሞተ ጊዜ አውጥታ በእግዚአብሔር ነቢይ ዐልጋ ላይ አስተኛችው ዘግታበትም ወጣች። ባሏንም ጠርታ ወደ እግዚአብሔር ነቢይ እሔዳለሁና አንድ አህያና ከብላቴኖች አንድ ብላቴና ስደድልኝ አለችው። ባሏም መባቻ ያይደለ ቅዳሜ ያይደለ ዛሬ ለምን ትሔጃለሽ አላት እጅ እነሣው ዘንድ እሔዳለሁ አለችው። አህያውንም ጫኑላት አገልጋይዋንም ተነሥ እንሒድ ባልኩህ ጊዜ መሔድን አትከልክለኝ ና ተከተለኝና ወደ እግዚአብሔር ነቢይ ወደ ቀርሜሎስ እንሒድ አለችውና ሔደች።

ኤልሳዕም ያቺን ሴት ስትመጣ በአያት ጊዜ ብላቴናው ግያዝን ያቺ ሴት ሱማናዊቷ ሴት ናት። አሁንም ሩጠህ ሒደህ ተቀበላት ደኅና ነሽን ባልሽስ ደኅና ነውን ልጅሽስ ደኅና ነውን በላት አለው እርሷም ደኅና አለችው። ወደ ኤልሳዕም ዘንድ ወደ ተራራው ደርሳ እግሩን ያዘችው ግያዝም ሊከለክላት መጣ ኤልሳዕም ሰውነቷ አዝናለችና ተዋት እግዚአብሔር ግን ነገሩን ሠውሮኛልና አልነገረኝም አለው። አታሰቅቀኝ ያልኩህ አይደለምን በውኑ እኔ ከአንተ ከጌታዬ ልጅን የለመንኩት መለመን አለን አለችው።

አልሳዕም ግያዝን ወገብህን ታጠቅ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሒድ ሰውም ብታገኝ እንዴትነህ አትበለው እንዴት ነህ ቢልህም አትመልስለት በትሬንም በሕፃኑ ግንባር ላይ አስቀምጣት አለው። የዚያም ሕፃን እናት እንዳልተውህ ሕያው እግዚአብሔርን በረከትህን አለችው ኤልሳዕም ተነሥቶ አብሮአት ሔደ። ግያዝም በፊታቸው ይሔድ ነበር ሩጦም ቀደማቸው በትሩንም በዚያ ልጅ ግንባር ላይ ጣላት ነገር ግን አልሰማውም አልተናገረውም ግያዝም ተመልሶ ኤልሳዕን ተቀብሎ ያ ልጅ አልተነሣም አለው።

ኤልሳዕም ወደ ቤት ገብቶ ሕፃኑን ሙቶ በዐልጋ ላይ ተኝቶ አገኘው በሁለታቸውም ላይ ደጃፉን ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ወደ ዐልጋውም ላይ ወጥቶ በዚያ ሕፃን ላይ ተኛ አፉን በአፉ ላይ ዐይኖቹን በዐይኖቹ ላይ እጆቹንም በእጆቹ ላይ አድርጎ በላዩ ላይ ተኛ የዚያም ልጅ ሰውነት ሞቀ።

ከዚህ በኋላ ተነሥቶ በቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ተመላለሰ ዳግመኛም ወጥቶ በዚያ ልጅ ላይ ተኛ እስከ ሰባት ጊዜ እንዲህ አደረገ ከዚያም በኋላ ያ ልጅ ዐይኑን ገለጠ ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ ያቺን ሱማናዊት ሴት ጥራት አለው።

ጠርቷትም ወደርሱ ገባች ኤልሳዕም እነሆ ልጅሽን ውሰጂ አላት እርሷም ከእግሩ ላይ ወድቃ ሰገደችለት ልጅዋንም ይዛ ወጣች። የሶርያ ሰው ንእማንም ወደርሱ በመጣ ጊዜ በዮርዳኖስ ውኃ ከለምጹ አዳነው ንእማንም ብዙ እጅ መንሻ ወርቅና ብር ልብሶችንም አመጣለት ከእርሱም ምንም ምን አልወሰደም።

ደቀ መዝሙሩ ግያዝም ተደፋፍሮ ንእማንን ተከተለው ምክንያትም ፈጥሮ ንእማንን እንዲህ አለው ከኤፍሬም አገር ከነቢያት ልጆች ሁለት ሰዎች መጥተውብኛልና አንድ መክሊት ብርና ሁለት ልብሶች ስጣቸው ብሎሃል አለው ንእማንም ሁለት መክሊቶችንና ሁለት ልብሶችን ሰጠው።

ኤልሳዕም ግያዝ ያደረገውን አውቆ ረገመው የንእማንም ለምጽ ገንዘብ ወዳጅ በሆነው በግያዝ ላይ ተመለሰ። በሰማርያም ረኃብ ጸና ከሶርያ ሰዎች የተነሳ የአህያ መንጋጋ በአምሳ ወቄት ብር እስቲለወጥ ድረስ ኵስሐ ርግብም የድርጎ አራተኛ በአምስት ብር እስቲሸመት ድረስ በሀገራቸው የሶርያ ሰዎች ሰፍረው ተቀመጡ። በዚህ ነቢይ ጸሎትም በአንዲት ቀን ረኃቡ ተለወጠ ጥጋብም ሆነ። በዘመኑም ብዙ ድንቆችና ተአምራቶችን አደረገ በሞተም ጊዜ በመቃብር ውስጥ አኖሩት በዚያም ወራት የሞአብ ሰዎች አገራቸውን ከበቡ። ይቀብሩም ዘንድ ሌላ ሰውን አመጡ አደጋ ጣዮችንም በአዩ ጊዜ የዚያን ሰው ሬሳ በኤልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት የዚያም ሰው ሬሳ በኤልሳዕ ዐፅም ላይ ወረደ የኤልሳዕንም ዐፅም በነካው ጊዜ ያ በድን ድኖ በእግሮቹ ቆመ።

@mezmurochh