Get Mystery Box with random crypto!

#ኅዳር_6 #ደብረ_ቁስቋም ኅዳር ስድስት በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከ | መዝሙረ ዳዊት

#ኅዳር_6

#ደብረ_ቁስቋም

ኅዳር ስድስት በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ዐረፉ፡፡

አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ከስደት በተመለሰች ጊዜ እንዲህ ሆነ፡- የብርሃን እናቱ ክብርት እመቤታችን ልጇን ይዛ ከእነ ዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ስትሰደድ ግብፅ ደርሰው በዚያ ቢቀመጡም ነገርን ግብፅ አልተመቸቻውም፡፡ ሕዝቡም በሰላም አልተቀበላቸውም፡፡ እንዲያውም በምድረ ግብፅ ብዙ ተሠቃይተዋል፡፡ ከግብፅም ተነሥተው ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላምና በፍቅር ተቀበላቸው፡፡ ከመንገዱና ከርሃብ ጥሙ ጽናት የተነሣ እጅግ ደክማለችና የኢትዮጵያ ሰዎች እመቤታችንን አይተው እጅግ አዘኑላት፡፡ ‹‹ይህችስ የነገሥታት ዘር ትመሥላለች ነገር ግን አንዳች ችግር አጋጥሟት ተሰዳ ወደ ሀገራችን መጥታለች..›› ብለው እንክብካቤን አደረጉላት፡፡ እግራቸውን አጥበው በክብር ማረፊያዎች ላይ አሳረፏቸው፡፡ መልካም መስተንግዶም አደረጉላቸው፡፡ እመቤታችንም ከድካሟ ካረፈች በኋላ ሀገሪቱን በእጅጉ ወደደቻትና የተወደደ ልጇን ‹‹ይህን ሀገርና ሕዝቧን በመላ ወድጃቸዋልሁና በዚህ እስከ መጨረሻው እንኑር›› አለችው፡፡ ጌታችንም ክብርት እናቱን ‹‹ይህች ቅድስት ሀገር ናት፣ በኋለኛው ዘመን የቅዱሳን መነኮሳት ቦታ ትሆናለች፡፡ በውስጧም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እመሰገንባታለሁ፤ የአንቺም ስም ሳይጠራ አይውልባትም›› አላት፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ደመና ጠቅሶ በእርሷ ላይ ተቀመጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤልም መጣና እየመራቸው መላ ኢትዮጵያን ጎበኟት፡፡ እመቤታችንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ወዳቸዋለች ደስም ተሰኝታባቸዋለችና ጌታችን ለክብርት እናቱ ‹‹ይህችን ቅድስት ሀገር አሥራት አድርጌ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም እጅግ ተደስታ ‹‹ልጄ አምላኬ›› ብላ አመሰገነችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ እየተዘዋወሩ መላዋ ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባረኳት፡፡ ጌታችንም ‹‹በዚህ ቦታ እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል፤ እከሌ የሚባል እንዲህ ዓይነት ቅዱስ ይነሣል…›› እያለ ብዙ ምሥጢራትን ለክብርት እናቱ ነገራት፡፡ ከዚህም በኋላ የስደቱ ዘመን ሲያልፍ ሄሮድስም በመጨረሻ ክፉ አሟሟትን ሲሞት መልአኩ ወደ ገሊላ አውራጃ እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ከዚህች ሀገርስ ባንሄድ እመርጣለሁ›› ስትለው የተወደደ ልጇ ግን ‹‹እናቴ ሆይ ጽድቅንና ፈቃድን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ብሎ አጽናናትና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡

ተመልሰውም ሊሄዱ ሲነሡ የኢትዮጵያ ሰዎች ልዩ ልዩ አምሐ እጅ መንሻ ሰጧቸው፡፡ ልዩ ልዩ ልብሶች፣ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ሽቱ እና ሥንቀቸውን በግመሎች ላይ ጭነው እመቤታችንንና የተወደደ ልጇንም በበቅሎ ላይ አስቀምጠው በክብር ሸኟቸው፡፡ እመቤታችንም ልጇን ታቅፋ በበቅሎ ተቀምጣ በበረሃው በመጓዝ ወደ መጣችበት አገር ሄደች፡፡ ኢትዮጵያንም የሰጧትን ብዙ እጅ መንሻዎች በግመሎች ጭና ይዛ ወደ አገሯ በተመለሰች ጊዜ ከአንድ ባሕር ዳር ደረሰች፡፡ ከዚያም የጀልባውን ባለቤት ‹‹እግዚአብሔርን ስለመውደድ አሻግረኝ›› ብላ ለመነችው፡፡ ባለጀልባውም ‹‹እነሆ ዕቃ የተጫኑ አምስት ግመሎችና ከአንቺ ጋር ከዚህም ሕፃን ጭምር አምስት ሰዎች እመለከታለሁ፣ አንቺ የተቀመጥሽባት በቅሎም አለች፡፡ ጀልባዋም ታናሽ ናት፣ የመቀመጫ ክፍሏም በውስጧ የተሳፈሩት ሰዎችም ተጨናንቀው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እንዴት ላሻግርሽ እችላለሁ? ነገር ግን እመቤቴ ሆይ! ይቅርታ አድርጊልኝ ይህን በክፋት አላደረግሁትምና›› አላት፡፡

ክብርት እመቤታችንም የጀልባው ባለቤት ሊያሻግራት እንዳልቻለ በተረዳች ጊዜ ‹‹ልጄ ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆንህ ይህን ትልቅ ወንዝ ለመሻገር የአምላክነትህን ሥራ ትሠራ ዘንድ እለምንሃለሁ›› ስትል ማለደችው፡፡ ያንጊዜም ጌታችን ክብርት እናቱን ‹‹የወለደሽኝ እናቴ ሆይ! አትዘኝ›› ብሎ አረጋጋት፡፡ ዳግመኛም ‹‹በእኔ ፈቃድ በአባቴ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ካንቺ ሰው ሆኛለሁና ሰው መሆኔንም ከአባቴ በቀር መስተፍሥሒ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም በቀር ያወቀ የለም፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ለሁሉም እንደየሥራው እከፍለው ዘንድ እመጣለሁ፡፡ ያችንም ሰዓት የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ የአዳም ልጆችም ቢሆኑም ከእኔና ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስም በቀር የሚያውቃት የለም፡፡ ያንጊዜ ‹ዐመፅን የሚናገር አንደበት ሁሉ ይዘጋል› ብሎ አባትሽ ዳዊት እንደተናገረ እከራከራለሁ የሚል አንደበት እንደድዳ ምላሽ ያጣል›› አላት፡፡

ክብርት እመቤታችን ማርያምም ይህንን ሁሉ ምሥጢር የተወደደ ልጇ የነገራትን ታስተውለው በልቧም ትጠብቀው ነበር፡፡ ጌታችንም አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለክብርት እናቱ ይህንን ከነገራት በኋላ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ከወንዙ ማዶ ጢር በሚባል ተራራ ያሉትን ድንጋዮች ጠቀሳቸው፡፡ ያንጊዜም እነዚህ ድንጋዮች እየተገለባበጡ መጥተው እንደ ጀልባ ሆነው በወራጁ ወንዝ ላይ ተንሳፈፉ፡፡ ከዚያም እመቤታችንን ከሕፃኑ ጋር ከነቤተሰቧና ከነጓዟ አሻገረሯት፡፡

እነዚህንም ድንጋዮች ያዩ ሰዎች ሁሉ እጅግ አድንቀው ‹‹ብቻውን ድንቅ ተአምራት ያደረገ፣ እስራኤልን የፈጠረ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን የጌትነቱም ስም የተመሰገነ ነው›› እያሉ አመሰገኑ፡፡ እነዚህም የተባረኩ ሰዎች ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ በዚህች አገር ለስምንት ቀን ተቀመጡ፡፡ ከዚህም በኋላ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ስለደረገላት መልካም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽማ እያመሰገነች ወደ አባቷ ወደ ዳዊት አገር ተመለሰች፡፡

ዳግመኛም በኋለኛው ዘመን ጌታችን በዚህ በደብረ ቍስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸውና ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ የቍርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነገር የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮቹ ሆኑ፡፡

(ስንክሳር ዘተዋህዶ እና #ገድላት_አንደበት)