2021-04-24 11:16:16
#በእርሱ #ቊስል #እኛ #ተፈወስን
ጲላጦስም የካህናት አለቆችንና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህንን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት እነሆም በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም፡፡ ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም ወደ እኛ መልሶታልና እነሆም ለሞት የሚያደርሰው ምንም #አላደረገም፡፡ እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ አላቸው (ሉቃ. ፳፫፥፲፬‐፲፮)
ጲላጦስ የጌታችንን ንጹሕ መሆን ካወቀ በኋላ ቀጥቼ #እፈታዋለሁ አለ፡፡ ንጹሕ በመሆኑ ምክንያት የተቀጣ #ከጌታችን በቀር ማን አለ? ጲላጦስ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ስለፈለገ ያን ሁሉ ጥያቄና መልስና ሕጋዊውን የፍርድ ሒደት ማስፈጸም ትቶ በንጹሑ ጌታ ላይ ግርፋት እንዲወርድበት ፈረደ፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ #በውርደቱ ፍርዱ #ተወገደ ብሎ #እንደተናገረው ትንቢት ጲላጦስ በእርጋታ ጀምሮት የነበረውን ሕጋዊ የምርመራና የፍርድ ሒደት አሽቀንጥሮ ጥሎ (አስወግዶ) ከሕግ ውጪ በዚያች ቀን በአይሁድ እጅ የተዋረደውን ጌታ ያለ ፍትሕ እንዲገረፍ ወሰነበት፡፡ (ሐዋ. ፰፥፴፫)
ጲላጦስ #ኢየሱስን ይዞ #ገረፈው (ዮሐ. ፲፱፥፩) የጲላጦስ አሳብ #በመሰቀሉ ፈንታ ግርፋት ቢገረፍ ሕይወቱን ካዳንኩለት #ቢቆስል ምንም አይደለም የሚል ነበር፡፡ አይሁድም የግርፋቱን ጽናት አይተው ይሙት ማለታቸው እንደሚቀር ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከትናንት ምሽት ጀምሮ ታስሮ ሲንገላታ ያመሸውን ፣ በሐናና ቀያፋ ግቢ ውስጥ ሲደበደብና በጡጫ ሲመታ ያደረውን ጌታ በምሕረት የለሾቹ የሮም ወታደሮች እጅ እንዲገረፍ አሳልፎ #ሠጠው፡፡
የሮማውያን ግርፋት እንደ አይሁድ ግርፋት በጅራፍ ብቻ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ ዘቂሣርያ እንደገለጠው ጅራፉ በቆዳ ከተሠራ በኋላ በላዩ ላይ ስለታማ የሆኑ የብረት ኳሶች ሾለው የተሳሉ የአጥንት ስብርባሪዎች ይደረጉበታል፡፡ በዚህ አሰቃቂ የግርፋት መሣሪያና በጨካኞቹ ወታደሮች እጅ ወድቀው ሥቃዩን መቋቋም ተስኖአቸው የሞቱም ብዙዎች ናቸው፡፡
በጅራፉ ላይ የተሠሩት የብረት ኳሶችና የአጥንት ስብርባሪዎች በሚገረፈው ሰውነት ላይ ሲያርፉ ሥጋውን እየነጩ የሚነሡ ስለሆኑ ጅራፉ በሰውነት ላይ ማረፉ ብቻ ሳይሆን ከሰውነት ላይ የሚነሣበትም ቅጽበት እጅግ ለመግለጽ የሚከብድ ሥቃይ የሚያደርስ ነው፡፡ የግርፋቱ መጠን በጨመረ ቁጥር የደም ሥሮችና #አጥንቶች እስከሚታዩ ድረስ የሚጎዳ ፣ የጎድን አጥንቶችን መሰባበር ፣ ከፍተኛ የሆነ ውጪያዊና ውስጣዊ የደም መፍሰስ ፣ የሳንባ መጎዳት የሚያስከትል አሰቃቂ ሒደት ነው፡፡
በዚያች ቀን #ጌታችንን ለመግረፍ የተመደቡት ወታደሮች እስራኤልን በብርሃን ዓምድ በሌሊት የመራቸውን #አምላክ #ሙሴና #አሮንን #በደመና ዓምድ ያነጋገራቸውን አምላክ በድንጋይ ዓምድ ላይ ለመግረፍ ዕርቃኑን #አሰሩት፡፡ የካህናት አለቆችን ደስ ለማሰኘት ሲሉም በሙሉ ኃይላቸው በታላቅ ጭካኔ እጅግ ብዙ ግርፋትን አዘነቡበት፡፡ አንድ ገጣሚ እንዳለው በሙሴ አድሮ #የፈጣሪን ክብር ለማየት የለመነው የሰው ልጅ ፈጣሪ በጊዜው #ጀርባዬን #ታያለህ ብሎ የገባለትን ቃል ቢፈጽምለትና ጀርባውን ቢያሳየው ግርፋትን አዘነበበት፡፡ (ዘጸ. ፴፫፥፳፫) በእርግጥም ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ #ከጲላጦስ ግርፋትን ይቀበልበት ዘንድ ጀርባን ፈጠረ እንዳለው አምላክ ሰው የሆነውና ጀርባን ለራሱ ያዘጋጀው ስለ ሁላችን #ኃጢአትን #ግርፋትን ሊቀበልበት ነበር፡፡
የሮማውያን ግርፋት ቅዱስ ጳውሎስ እንደተገረፈው እንደ አይሁድ ግርፋት በመጠን ተወስኖ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ› እያለ የተገረፈው ሰው በሕይወት ተርፎ እያስታወሰ የሚናገረው ዓይነት ግርፋት አይደለም፡፡ (፪ቆሮ. ፲፩፥፳፬)
ቤተ ክርስቲያናችን #የጌታችን ግርፋት #ስድስት #ሺህ #ስድስት #መቶ #ስድሳ #ስድስት ጊዜ እንደሆነ ስታስተምር አምስት ሺህ ነው ፣ አራት ሺህ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህን አሰቃቂ ግርፋት በሺህ ለሚቆጠር ጊዜ መገረፉን ግን ሁሉም ሊቃውንትና የታሪክ ሰዎች ተስማምተውበታል፡፡ ጌታችን እጅግ መገረፉን የሚያሳየን መስቀሉን ባሸከሙት ጊዜ በየሥፍራው እስኪወድቅ ድረስ አቅም ማጣቱ ነው፡፡
የጌታን ግርፋቱንስ መቁጠር ቢቻልም እንኳን ሥቃዩን ግን እንዴት ልንቆጥረው እንችላለን? ቤተ ክርስቲያናችን ከሥጋው አልፎ አጥንቶቹ እስከሚታዩ ድረስ ስለ ተገረፈው አምላክ በዕለተ ዓርብ የምታነበውና የምታዜመው ራሱ #ክርስቶስ አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት አድሮ ስለሕማሙ የተናገረው የትንቢት ቃል የሥቃዩ መጠን ጥቂትም ቢሆን ለማሰብ ያግዘናል፡-
‹‹እንደ ውኃ ፈሰስሁ #አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ ፤
ልቤ እንደ ሰም ሆነ #በአንጀቴም መካከል ቀለጠ…
#አጥንቶቼ ሁሉ #ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ #ተመለከቱኝም …
#አጥንቶቼ #ተነዋወጡ (መዝ. ፳፪፥፲፬፣፲፯፤፴፩፥፲)
ቅዳሴያችን እንዲህ ይላል #የወልድን መከራውን የሚናገር ምን ዓይነት አፍ ነው? ምን ዓይነት #ከንፈር ነው? ምን ዓይነት አንደበት ነው? #የፍቅር #ጌታ #ሕማማቱ በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል ፤ ሕሊናም ይመታል #ነፍስም #ትንቀጠቀጣለች #ሥጋም #ይደክማል በእውነትም #የጌታችንን ሥቃይ ለመግለጽ ምንም ዓይነት ቋንቋ ምንም ያህል ቅኔ አቅም አይኖረውም፡፡
ቅዱስ ኤፍሬምም :-
#በክርስቶስ #የተወደዳችሁ ሆይ ኑ! ወዲህ ቅረቡ በዚች ዕለት በዳዊት ከተማ የሆነውን አብረን እንይ #በተስፋው ቃል ሲጠበቁ የነበሩት የተመረጡት #የአብርሃም #ዘሮች ዛሬ ምን እንዳደረጉ እንመልከት! ጌታ ሆይ ረዥሙን ሥቃይህን ማን ሊገልጸው ይችላል?›› ይላል፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው #ስለ #እኛኃጢአት ነበር፡፡ ኦሪት የሚገረፍ ሰው ‹‹የግርፋቱም ቊጥር እንደ ኃጢአቱ መጠን ይሁን›› ትላለች፡፡ (ዘዳ.፳፭፥፪) ጌታችን ማንም ስለ ኃጢአቱ ሊወቅሰው የማይችል ንጹሕ ቢሆንም #እግዚአብሔር #የሁላችንን #በደል #በእርሱ ላይ #አኖረ ስለተባለ ግርፋቱም በተሸከመው የእኛ ኃጢአት መጠን ሆነ፡፡
እርሱ #ስለመተላለፋችን #ቈሰለ ስለ በደላችንም ደቀቀ #የደኅንነታችንም ተግሣፅ #በእርሱ ላይ #ነበረ በአጋንንት እጅ ልትገረፍ የጸጋ ልብስዋን አውልቃ ዕርቃንዋን በሲኦል የወደቀች ነፍሳችንን ነጻ ያወጣት ዘንድ እርሱ በጨካኝ ወታደሮች እጅ #ዕርቃኑን #ተገረፈ፡፡
እኛን #ከሚገባን #ግርፋት ያድነን ዘንድ #ኢየሱስ የማይገባውን ግርፋት #ተገረፈ የተገረፈባቸውም አለንጋና ገመድ በደም ታለሉ ተነከሩ ከግርፋቱ ጽናት የተነሣ ሥጋው ሁሉ አለቀ #ሐዋርያው #ጴጥሮስ በመገረፉ ቊስል ተፈወሳችሁ በማለት እንደተናገረ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን (፩ጴጥ. ፪፥፳፬፤ኢሳ. ፶፫፥፭)
#ህማማት #በዲያቆ #ሄኖክ #ሀይሌ
129.1K views08:16