Get Mystery Box with random crypto!

እኔ ሆዬ የጨላ ከረጢቴን አጥብቄ እንደያዝኩ አንድ ሐሳብ አወጣ አወርድ ጀመር፡፡ ጌታችሁም ሐዋርያት | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

እኔ ሆዬ የጨላ ከረጢቴን አጥብቄ እንደያዝኩ አንድ ሐሳብ አወጣ አወርድ ጀመር፡፡ ጌታችሁም ሐዋርያትን ለማረጋጋት እኔ እንጂ እነሱ አሳልፈው እንደማይሰጡት እንደማይሸጡት ለማሳወቅ ‹‹እኔ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው›› ብሎ ለእኔ ሰጠኝ፡፡ ይገርማቹኃል ያኔ በገንዘብ ፍቅር የገባው ሳይሆን ዋናው ሰይጣን በልቤ ገባ፡፡

ስፖንሰሬን ልብ አላችሁ? ጌታችሁም ‹‹የምታደርገውን ቶሎ አድርግ›› አለኝ፡፡ ጌታችሁ እንዲህ ሲለኝ ሐዋርያት አልባነኑም ነበር፡፡ እነሱ ጌታቸው ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ነገር እንድገዛ ለድሆች እንድመጸውት ያዘዘኝ ነው የመሰላቸው፡፡ አይገርምላችሁም! ካላመናችሁ ዮሐ 13÷29 አንብቡ፡፡ ያኔ ሰይጣን እራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ወሰወሰኝ፣ ጌታችሁን ሽጥ ሽጥ አለኝ፡፡

የሚገርማቹ ሰው እንደ ዕቃ መሸጥ ባልተለመደበት እንዴት ጌታችሁን እንደሸጥኩት እስከ ዛሬ ይገርመኛል፡፡ ምን ላድርግ ትንቢት ነዋ፡፡ ደግሞም የጨላዋ ከረጢት በእጄ እያለች ጌታችሁን ለመሸጥ መሯሯጤ ዛሬም ምን ነክቶኝ ነው እላለሁ፡፡ ግን ትንቢት ነዋ፡፡

ብዙዎች ‹‹ጌታህን ለምን በሠላሳ ብር ብቻ ሸጥከው›› ይሉኛል፡፡ ትንቢቱ እንዳለ ሆኖ ዮሴፍ የሚባል ጻድቅ ሰው ወንድሞቹ በሃያ ብር ሽጠውት እንደነበር ሰምቻለሁ። ከዮሴፍ ላስበልጠው ብየ ነው በሠላሳ ብር የሸጥኩት፡፡ ደግሞም እኔ ሆኜ ነው ሠላሳ ብር የሸጥኩት፡፡ አይሁድ ጌታችሁን ይጠሉት ስለነበር እንኳን ሠላሳ ብር አንድ ብርም አይሸጡትም ነበር፡፡

እውነት እናውራ ከተባለ "ይሁዳ ጌታውን ሸጠ" ትላላችሁ። እናንተ ጌታችሁን ስንቴ ሽጣቹኃል? ስንቴ ክዳቹታል? ስንቴ በድላቹታል? ስንቴ ሕጉን አፍርሳቹኃል? በቤተ ክርስቲያን እያገለገለ ሰዉግ በመተት የሚያሰቃየው መተተኛ ኃጢአቱ ከእኔ ቢብስ እንጂ የሚያንስ አይደለም።

በቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ እየተመላለሱ መተት የሚመትቱ እኮ ከእኔ የባሰ ጌታቸውን የካዱ ናቸው። ሙዳየ መጽዋት የሚገለብጡት፣ ከቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የሚዘርፉት አገልጋይ ተብዬዎች በምን ሞራላቸው ነው "ይሁዳ ጌታውን በሠላሳ ብር ሸጠ" ብለው የሚናገሩ የሚያስተምሩ? ስለ እውነት ፍረዱ!

እኔ አንዴ ነው ጌታችሁን የሸጥኩት የካድኩት። መቶ ጊዜ ጌታችሁን የካዳችሁ፣ የሸጣችሁ የላችሁም? እኔ ጌታችሁን አንዴ ነው ያሳዘንኩት የካድኩት። እናንተ ጌታችሁን ስንት ጊዜ አሳዝናቹኃል ክዳቹኃል? ትንቢት ሳይነገርባችሁ ትንቢት የምትፈጽሙ አይደላችሁ?

በእውነት ጌታችሁ በዚህ ዘመን ሊሰቀል ቢመጣ እንደው ስንት ብር ትሸጡት ነበር? በዳይሬክት ነው ወይስ በጨረታ? ደላሎችስ ስንት ብር በጌታችሁ ላይ ፈርቅ ትይዙ ነበር? የሚስማር ፋብሪካዎች ‹‹እኔ ከንጽህ ብረት የተዘጋጀ ምርጥ ሚስማር ችንካር አቀርባለሁ›› ይላል፡፡

አንዱ የእንጨት ፋብሪካ ‹‹እኔ ለስቅላት የሚያመች፣ እጅ እግር ከወርች የሚያስቸነክር ጠንካራና ጌታን የሚሸከም መስቀልኛ እንጨት አቀርባለሁ›› ይላል፡፡

አንዱ የቆዳ ፋብሪካ ‹‹ተረፈ ምርት ከሆነው ቆዳ ደንበኛ ሥጋን የሚያሳርር ደንበኛ መግረፊያ ጠፍር አቀርባለሁ›› ይላል፡፡ እናንተስ ስቃዩን እንደ ዮሐንስ እያለቀሳችሁ ከማየት ይልቅ ሰልፊ ለመነሳት አይደል የምትሯሯጡት?

ፎቶውን በፌስ ቡክ፣ በኢንስታ ግራም ወዘተ ላይ ፖስት ለማድረግ እንጂ ፎቶውን እያያችሁ ለማንባት አትቸኩሉ፡፡ ብቻ ጉድ ነው!

ከዛማ ጌታችሁንና ሐዋርያትን ትቼ ጌታችሁን ለመሸጥ ገዢ ፍለጋ ወጣሁ፡፡ ስበር ስከንፍ ሄጄ የአይሁድ አለቆችን አገኘሁ፡፡ እኔም ‹‹እንደ ጠላት የምታዩትን ሰው አሳልፌ እሰጣችኃለሁ ምን ትሰጡኛላችሁ›› አልኳቸው፡፡

እነሱም የጨላ ነገር እንደማይሆንልኝ ማን እንደነገራቸው አላውቅም ‹‹ሠላሳ ብር እንገጭኃለን አንተ ብቻ አሳልፈህ ስጠን›› አሉኝ፡፡ እኔም ተስማማሁ፡፡ ሠላሳ ብር ገጩኝ፡፡ ከዛማ በቃ ጌታችሁን ለመሸጥ ቀብዲ ኸረ የምን ቀብዲ ሙሉ ክፍያውን ተቀብዬ ጌታችሁን አሳልፌ የምሰጥበትን መንገድ ማሰብ ሥራዬ ሆነ፡፡

አንድ ቀን ጌታችሁ እኔን ሳይጨምር ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ሊጸልይ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፡፡ ይህ ቦታ ጌታችሁ እንደሚውልበት እንደሚያድርበት አውቅ ስለነበር ከዚህ የበለጠ ምቹ ጊዜ አላገኝም ብዬ የአይሁድ አለቆችንና ወታደሮችን አስከትለን እሱ ወደለበት ሄድን፡፡

አይሁድም ‹‹እሱን በምን እናውቃለን›› አሉኝ። አይሁድ ይህን ያሉት ጌታችሁ እና የድሮ ጓደኛዬ ዮሐንስ በመልክ ስለሚመሳሰሉ መለየት ስለማይችሉ ነው። እኔም ‹‹ቀጥታ ሄጄ የምስመው እርሱ ስለሆነ ያኔ ያዙት›› ብዬ ነገርኳቸው፡፡

ይገርማቹኃል ጌታችሁ እኔን ሲያይ ፊቱ ላይ ያለው የፍቅር ፈገግታው አሁንም በሲኦል ሆኜ አልረሳውም፡፡ ጌታ በፍቅር ሲቀበለኝ እኔ በተንኮል መሳም ሳምኩት። እሱም ስላወቀብኝ ‹‹ይሁዳ ሆይ፣ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህ›› ሲለኝ አንጀቴ ሳይሆን ነፍሴ ተላወሰች፡፡

ግን ምን ላድርግ እኔ ጌታችሁን አሳልፌ የሰጠሁት ስስመው ሳይሆን ሠላሳ ብር ስቀበለው ስለሆነ አሳልፌ ሰጠሁት፡፡ ዛሬም እናንተ ጌታችሁ የሰጣችሁን ጸጋ፣ ክብር፣ አደራ፣ ታማኝነት፣ እምነት ለኃጢአት/ለሰይጣን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ፡፡

ጌታችሁን ሲያንገላቱት ሲመቱት ሳይ አንዳች ነገር ተሰማኝ፡፡ ገንዘብ ወዳድነቴ፣ ሌባነቴ፣ ከሃዲነቴ፣ እምነት አጉዳይነቴ፣ ላመነኝ ጌታችሁ አለመታመኔን ሳስብ ወዲያው የአይሁድ አለቆች ጋር ሄጄ ‹‹ንጽህ ደም አሳልፌ በመስጠት በድያለሁ›› ብዬ በጸጸት ተናገርኩ።

ሠላሳ ብሩንም ውሰዱ አልኩ፡፡ እነሱም ‹‹አንተው ተጠንቀቅ እራስህ ተወጣው›› አሉኝ፡፡ እኔም ጌታችሁን የሸጥኩበትን ሠላሳ ብር በቤተ መቅደስ ጥዬ ሄድኩ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ፈራጆች ሠላሳ ብሩን ላልበላው ላልጠቀምበት ነው ጌታችሁን የሸጥኩት። በቃ ትንቢት ነዋ! ባደረኩት ነገር እራሴን ወቅሼ ለማረጋጋት ባለመቻሌ ለእኔ ሞት ይገባኛል ብዬ እራሴን ሰቅዬ አጠፋሁ፡፡

ግን አንድ ነገር ልብ በሉ፡፡ ብዙ ሰው ጌታችሁን መሸጤን እንጂ ክፍኛ መጸጸቴን ልብ አይሉም፡፡ በእጃችሁ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ጸጸቴን አስመልክቶ ‹‹ተጸጸተ›› ብሎ መስክሮልኛል ደግሞም ጸጸቴ የእውነት ሳይሆን የውሸት ቢሆን ኖሮ የእውነት ቃልን የያዘው ቅዱሱ መጽሐፍ ‹‹ተጸጸተ›› ብሎ አይመሰክርልኝም ነበር፡፡ በእውነት መጸጸቴን ካላመናችሁ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27፥ 3 አንብቡ!

ታድያ እናንተ በሠራችሁት ስህተት እና ኃጢአት እንደ እኔ ተጸጽታችሁ ታውቃላችሁ? ብትጸጸቱማ ከስንት የክፋት መንገዳችሁ፤ ከስንት የዝሙት ወዘተ የኃጢአት ሕይወታችሁ ትመለሱ ነበር፡፡ ግን ማትመለሱት ጸጸታችሁ ጊዜያዊ ስለሆነ ነው፡፡

ኤኒ ወይስ ጌታችሁን የሸጥኩበት ብር ለእኔም ለአይሁድም ሳይሆን አይሁድ ‹‹የደም ዋጋ ነው›› ብለው ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን መሬት ገዙበት፡፡ ያ የደም መሬት ዛሬም እስራኤልና ፍልስጥኤም ደም ሲፋሰሱበት ይኖራል፡፡ የዛሬ ሁለት ሺ ምናምን ዓመት ጌታችሁን የሸጥኩበት የሠላሳ ብር ገዳፋ፣ እስራኤልንና ፍልስጥኤምን ዛሬም ሲያዳፋ ይኖራል።

የሚያሳዝነው ያኔ ጌታችሁ እንደ ጴጥሮስ የሰጠኝን የንስሐ እድል ብጠቀምበት ኖሮ ዛሬ መኖርያዬ ሲኦል ሳይሆን ገነት ነበር፡፡ እራሴን ላጠፋ ዛፍ ላይ ስንጠለጠል ዛፍዋ ‹‹ይሁዳ ሆይ እንደ ወንድምህ እንደ ጴጥሮስ ንስሐ ግባ›› ስትለኝ አልሰማም አልኩኝ፡፡ ዛሬም ንስሐ ግቡ ሲባሉ የማይሰሙ እንደ እኔ የደነደነ ልብ ያላቸው ስንት አሉ፡፡