Get Mystery Box with random crypto!

የኩላሊት ጠጠር (Nephrolithiasis) ምንድን ነው? ብዙዎቻችን ውሀን የመጠጣት ባህላችን | Medical Laboratory

የኩላሊት ጠጠር (Nephrolithiasis) ምንድን ነው?

ብዙዎቻችን ውሀን የመጠጣት ባህላችን በጣም ዝቅ ያለ ነው። ይህ ልምድ ደሞ ብዙ መዘዝን ይዞብን ምጣቱ አይቀሬ ነው።

አንድ ወንድማችን "ኩላሊቴ በጠጠር ምክንያት ፈሳሽን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ አልቻለም እና ሀኪሞቹ አሁን መውጣት አይችልም ፣ ገና ነው የሚል መልስ ነው የሰጡኝ ፣ እና ለምንድን ነው" የሚል ጥያቄ አንስቶልኝ ነበር።

የኩላሊት ጠጠር በአብዛኛው ጊዜ 80% በውስጡ ካልሺየም ኦግዛሌት (calcium oxalete) የተቀሩት ደግሞ ከካልሺየም ፍስፌት (calcium phosphate) ፣ ዩሪክ አሲድ (uric acid) ፣ ሲስቲን (cystine) ሊሰሩ ይችላሉ።

የኩላሊት ጠጠር በአብዛኛው በአንድ ኩላሊት በኩል ይታያል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሁለቱም ኩላሊት ሊኖር ይችላል።

ለኩላሊት ጠጠር የሚያጋልጡን ነገሮችስ?

ለኩላሊት ጠጠር የመጋለጥ እድላችን የሚወሰነው ሽንት በተሰራበት (composition) ለምሳሌ በካልሼየም ኦግዛሌት የተሰራ ጠጠር ከሆነ በሽንት ወስጥ የሚገኝ ከፍተኛ መጠን ካልሺየም እና ኦግዛሌት ሲኖር እንዲሁም ዝቅተኛ ካልሽየም እና ፖታሺየም መውሰድ እና ፈሳሽ ነገር ያላቸው ምግቦች አለማዘውተር እንዲሁም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከስኳር የተሰሩ ጣፋጭ መጠጦች ተጋላጭነተን ይጨምረዋል ተብሎ ይታሰባል።

ሌሎች አጋላጭ ምክንያቶች ለምሳሌ አንድ ሰው ከዚህ በፊት የኩላሊት ጠጠር ከነበረበት ድጋሚ የመመለስ እድል ሊኖረው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ በዘር (በቤተሰብ) ወስጥ ጠጠር ያለበት ካለ ፣ በተደጋጋሚ የላይኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጠቂ መሆን ፣ መድሀኒቶች ለምሳሌ Idinavir, Acyclovir, Sulfadiazine፣ መድሀኒቶችን ከሚገባው መጠን በላይ መውሰድ፣ ከመጠን በላይ ውፍረት፣ ከመጠን በላይ በፕሮቲን እና Vitamin C የበለፀጉ ምግቦች መመገብ ፣ ከከመጠን በላይ የሰውነት እንቅስቃሴ ለምሳሌ የማራቶን ሯጮች ፣ ደም ግፊት ፣ ስኳር ፣ ሪህ ችግር ያለባቸው ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

ምልክቶቹስ?
- በአብዛኛው ከ20-60 ደቂቃ ሄድ መጣ የሚል ህመም በጎናችን አካባቢ ሊሰማን ይችላል። ህመሙ በጣም ሀይለኛ ውጋት ፣ ቁርጠት ስለሆነ ህመምተኛው የመንቆራጠጥ ነገር ሊያሳይ ይችላል።

አንዳንዴም ህመሙ እስከ ሽንት ፌኛ አካባቢ ሊደርስ ይችላል። ይህም አንደ ጠጠሩ ያለበት ቦታ ይወሰናል። ከዚህ በተጨማሪ የሽንት ቀለም ወደቀይነት (ደም) መቀላቀል ፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስመለስ ፣ ሽንት ማጥ ፣ ሽንት ማጣደፍ ሊኖር ይችላል።

ምርምራዎቹስ?
- ከላይ የጠቀስኳቸውን ምልክቶች በምናይበት ግዜ ቶሎ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ይጠበቅብናል። የጤና ባለሙያውም እንደ አስፈላጊነቱ የተለያዩ ምርመራዎችን ለምሳሌ የሽንት ምርመራ ፣ የሆድ አልትራሳውንድ ፣ የሆድ x ray ፣ የሆድ ሲቲ ስካን ፣ ሊያዝልን ይችላል

ነፍሰ ጡር እናት ላይ ምርመራዎችን ስናዝ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል። ምክንያቱም ከx-ray ፣ እና ሲቲ ስካን የሚወጣው ጨረር በተለይ ፅንሱን ሊጎዳው ስለሚችል ነው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ አልትራሳውንድ ተመራጭ ይሆናል።

የሚያመጣውስ ችግር?
-የኩላሊት ጠጠር ካልታከመ ለኢንፌክሽን ፣ ደጋሚ ተመልሶ የመምጣት ችግር (recurrence) ፣ የሽንት ቱቦ መዘጋት ፣ ኩላሊትን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እስከማድረስ ሊደርስ ይችላል።

ህክምናውስ?
- አመጋገባችንን ማስተካከል
- ጠጠሩን ያመጣብን ችግር ከታወቀ ማከም
- የህመም ስሜት ላላቸው ታካሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ የህመም ማስታገሻ ሊሰጥ ይችላል።

- ማንኛውም የኩላሊት ጠጠር በቀዶ ጥገና ይወጣል ማለት አይደለም። ይህም የሚወሰነው እነደ ጠጠሩ መጠን ሲሆን የጠጠሩ መጠን እስከ 10 ሚሊ ሜትር ከሆነ በሽንት እንዲወጣ ነው የሚመከረው። በዚህ ጊዜ ታካሚው ዉሀ በብዛት እንዲጠጣ ይመከራል መጠናቸው ከ10 ሚሊሜትር በላይ ከሆነ የመውጣት እድላቸው ጠባብ ስለሆነ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ሊጠበቅን ይችላል። ለምሳሌ በድምፅ እና በጨረር በመታገዝ ጠጠሩ እንዲሰባበር በማድረግ ከዛም ውሀ በመጠጠት በሽንት እንዲወጣ ይደረጋል አንዳንድ ጊዜም በቀዶ ጥገና መውጣት ሊያስፈልግ ይችላል።

የህክምና አማራጮቹ የሚወሰኑት በባለሙያው ስለሆነ ከባለሙያ የሚሰጡንን ምክሮች ማክበር ተገቢ ነው።

NB. ንፁህ ውሀ በብዛት መጠጣት ተነገሮ ከማያልቁት ጥቅሞች አነዱ በሰውነታችን ውስጥ ያሉ አላስፈላጊ ቆሻሻዎችን ባሉበት ተቀምጠው ጉዳት እንዳያስከትሉ እና ለማስወገድ እጅግ ጠቃሚ ስለሆነ ውሀ የመጠጣት ልምዳችንን ብናዳብር መልካም ነው።

ለወዳጅዎ ያጋሩ
ጤና ይብዛሎ!
ዶ/ር ኤርሚያስ ማሞ