Get Mystery Box with random crypto!

በርካታ ወገኖች ከሰሞኑ በተለቀቀው የአብን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ቪዲዮ ዙሪያ ጥያቄዎችን በል | Christian Tadele Tsegaye

በርካታ ወገኖች ከሰሞኑ በተለቀቀው የአብን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ቪዲዮ ዙሪያ ጥያቄዎችን በልዩ ልዩ መልኩ አቅርባችሁልኛል። ለያንዳንዳችሁ በተናጠል ምላሽ ለመስጠት ጊዜን የሚወስድ ሆኖ ስላገኘሁት ጥቅል ምላሽ መስጠት ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል።

የቪዲዮው በሚዲያ መዋል ተገቢነት፦

ከጠቅላላ ጉባዔ ውጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ቀረፃ ሲሰራለት እስከማስታውሰው ድረስ ይሄ የመጀመሪያው ነው። መቀረጹ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ለሕዝብ ይፋ ይሁንና በሚዲያ ይተላለፍ የሚለው ጉዳይ ግን የማዕከላዊ ኮሚቴውን ፈቃድና ይሁንታን የሚጠይቅ ነው። ይህ ደግሞ እንዳልሆነ ፍፁም እርግጠኛ ነኝ። ይተላለፍ ቢባል እንኳን ሙሉው ወይንም የተቆረጠ ካለም ይኸው ይዘት በማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ መጽደቅ ይጠበቅበት ነበር። የሚተላለፍበትን ሚዲያም የመምረጥ ኃላፊነቱ እንዲሁ ለግለሰቦች ነፃ ውሳኔ የተተወ አልነበረም።

(ለአማራዊ ክብር ብለን እንጂ እንዲተላለፍ ይሁንታን ባልሰጠንበት፤ በስብሰባው ፈቃድ ተሰጥቶት ቀረፃ ያላከናወነ ሚዲያም ተገቢውን ቅጣት ማስቀጣት ይቻል ነበር። የድርጅትን የጋራ ንብረት ለግል ጥቅም ማዋል ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ነውር ነው። በመንግስታዊ ተቋም ቢሆን በሙስና ወንጀል ያስቀጣል። የአብን ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን በሥራ ላይ ቢሆን ኖሮ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ላይ እርምጃ ይወስድ ነበር።)

ከሥልጣን ስለመልቀቅ ስለቀረበው ሞሽን፦ ሞሽኑን ያቀረቡት ሊቀመንበሩ ናቸው። የቀረበው ሞሽን እርሳቸውን ጨምሮ አብንን በሥራ አስፈፃሚነት የመሩ ግለሰቦች ከኃላፊነት እንዲወርዱ ነው። አንድ ሊቀመንበር ራሱን ከኃላፊነት ለማንሳት ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል። አዲስ ሊቀመንበር ሲመረጥ የራሱን ካቢኔ ያዋቅራል። ነባር አዲስ ሳይል ማዕከላዊ ኮሚቴው እስካፀደቀለት ድረስ እጩዎችን ማቅረብ መብቱ ነው። ይህን መብት መልቀቅ የሚፈልግ ተሰናባች ሊቀመንበር በሞሽን ሊገድብ አይገባም። ደንባችንም ማንኛውም አባል የመምረጥ መመረጥ መብት አለው የሚል ድንጋጌ አለው። ሊቀመንበሩ ከ2 ዙር በላይ አይመረጥም ከሚለው ውጭ ገደብ አላስቀመጠም። ስለሆነም የቀረበው ሞሽን ኢደንባዊ ነው ብዬ ሞግቻለሁ። ሆኖም በእለቱ የተሰበሰቡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሞሽኑን ሲደግፉት ብቻዬን ተቃውሜዋለሁ። በአብላጫ ድምጽ የፀደቀው ሞሽን ቀጣዩ ተግባር የነበረው አዲስ ሊቀመንበር መምረጥ ነበር። ይሁንና ሞሽኑን በጀርባ የተውኔት ልምምድ ይዘው የቀረቡ ግለሰቦች በሚመረጠው አዲስ ሊቀመንበር ማንነት ላይ መስማማት አልቻሉም ነበር። በዚህ ምክንያትም 31 ለ 1 በሆነ ፍፁም አብላጫ ድምጽ የፀደቀው ውሳኔ ተሽሮ እስከጉባዔ ድረስ የነበረው አመራር እንዲቀጥል በሁለት ዙር አስቂኝ ድራማ ተወሰነ። ዜናው በመንግስት ሚዲያዎች ጭምር ውሳኔውን ወስነን ከመቋጨታችን በፊት በሰበር ዜና ተዳረሰ። ሰበር ዜናውንና ድራማውን ባልወደውም በውሳኔው ግን ደስተኛ ነበርሁ።

ለምን ተደሰትሁ?

ባለፉት ዓመታት በጉልህ ሲነሱ ከነበሩ ቅሬታዎች አንዱ የድርጅቱ ላእላይ መዋቅሮች (ሥራ አስፈፃሚ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን) አካታችነት ይጎላቸዋል የሚለው ነው። አካታችነት ከአካባቢ፣ ከእምነት፣ ከፆታና አካል ጉዳተኝነትን ጨምሮ ልዩ ፍላጎቶችን ታሳቢ ያደረገ፤ በተጨባጭ የነበሩ ክፍተቶችን መሙላት የሚችል የአመራር ሪፎርም እንዲደረግ በእጅጉ እፈልግ ነበር። ይህ ደግሞ ሞሽኑ ተቀባይነት አግኝቶ ከነባሩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር ቢዋቀር ኖሮ ተግባራዊ አይሆንም ነበር።

ሞሽኑ በመውደቁ በዋነኝነት የተደሰትሁት ግን አሁን ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈፃሚና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በየደረጃው ያለው የአብን መዋቅር እና የመዋቅሩ ወኪል የሆነው የጠቅላላ ጉባያተኛ ፍላጎት የማያሟላ፣ ድርጅቱ በቀጣይ አገራችንና ሕዝባችን ከሚፈልጉት ትግል አኳያ አዳዲስ ፊቶችንና አቅሞችን የሚፈልግ በመሆኑ፤ ከምንም በላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ከእከከኝ ልከክልህ ጠበባ ሰርክል በመውጣት በውድድር በጉባኤው በቀጥታ እንዲመረጡ እፈልግ ስለነበረ ነው። ማዕከላዊ ኮሚቴውም መዋቅራዊ ውክልና ኖሮት እንዳዲስ እንዲመረጥ፤ በአዲስ ከሚመረጠው ማዕከላዊ ኮሚቴ በመዋቅሩ የታመነባቸው ብቃቱ ያላቸው የሥራ አስፈፃሚዎች እንዲመረጡ በብርቱ እፈልጋለሁ። ይህን ደግሞ የድራማው ደራሲዎች አይፈልጉትም። ምክንያቱም ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለመምጣት መዋቅራዊ ውክልና ያስፈልጋቸዋል። መዋቅሩ እንደማይወክላቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ለመሆን የጉባያተኛውን አብላጫ ድምጽ ማግኘት ግድ ይላቸዋል። ይህ ደግሞ በመርፌ ቀዳዳ መሽሎክ ሆኖባቸው ጉባኤ እስከመበተንና ጉባያተኛን «መንጋ» ብለው እስከመዝለፍ አድርሷቸዋል። የጠቅላላ ጉባኤ መጥራት በኤርታሌ ላይ በባዶ እግር የመራመድ ያህል ያስጨነቃቸውም ይኸው ነው። ይህ ፍርሃታቸው ጉባያተኛን እስከማሳሰርና በዲስፕሊን ክስ ሽፋን እስከማገድ አወላክፏቸዋል። የምንታገለው የጭቆና ሥርዓት እንኳን ያልደፈራቸውን ነውሮች ሁሉ ፈጽመዋል። መዋቅራችን ግን በፍፁም ጽናት፣ አስተውሎትና ታጋሽነት የጉባዔውን እለት ዛሬም በመጠባበቅ ላይ ነው።

ምን ፍለጋ ቪዲዮው ተለቀቀ?

በመንግስት ሚዲያዎች በሰበር ዜና የተለቀቀውን አስታወሳችሁት? አዎ፥ መልቀቅ ፈልገን አላስለቅቅ አሉን የተባለውን አስቂኝ ተውኔት በምልሰት ለመተወን ነው።

የድርጅት ውስጠ ፓርቲ ጉዳዮች ያላነሳኋቸው በተለይ ከኦዲት ጋር የተገናኙ በአስረጂ ሰነዶች የተደገፉ ወሳኝ ነጥቦች አሉ። ጠቅላላ ጉባዔውን እንደጌታ ምጽኣት የናፈቅሁትም ይኸንኑ ለድርጅት የመጨረሻ የሥልጣን አካል በማቅረብ ተገቢው ውሳኔ እንዲያርፍበት ከልብ በመሻት ነው።

በዚሁ አጋጣሚ መላው የአብን አባላት፣ መዋቅራችንና ደጋፊዎቻችን እስካሁን ላደረጋችሁት በወርቅ ቀለም የሚከተብ የተጋድሎ ታሪክ እጅጉን አመሰግናችኋለሁ። የእናንተ ትውልድ አካል በመሆኔም ኩራቴ የትየለሌ ነው። ተጋድሏችሁ ለፍሬ እንዲበቃም በጽኑ እመኛለሁ!