Get Mystery Box with random crypto!

የብልጽግና ፓርቲ ኢመንግስታዊነት እና ኢመደበኝነት! **** በአገር ጉዳይ ገዥው ፓርቲ ለብቻው ውሳ | Christian Tadele Tsegaye

የብልጽግና ፓርቲ ኢመንግስታዊነት እና ኢመደበኝነት!
****
በአገር ጉዳይ ገዥው ፓርቲ ለብቻው ውሳኔ እንዲያሳርፍ እና ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር ለብቻው እንዲደራደር መፍቀድ አገርን የፖለቲከኞች የግል ንብረት እንድትሆን መፍቀድ ነው። ለመንግስታዊ ስነስርዓቱ እንኳን ቢያንስ ጉዳዩ ወደ ፓርላማ ቀርቦ በምክርቤቱ በኩል ማለቅ የሚኖርባቸው ጉዳዮች መከናወን ነበረባቸው። ፓርላማው አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ማናቸውም ቡድን ጋር መገናኘት ወንጀልና በሕግ የሚያስጠይቅ ነው። መሰል ነገሮች ካሉ የፍትሕ ሚኒስቴር ክስ የመመስረት ሥልጣን ተሰጥቶታል። የፀጥታ ተቋማትም የፀረ ሽብር አዋጁ እንዲከበር በሕግ የተጣለባቸው ግዴታዎች አሉ።

ይሁንና የብልጽግና ፓርቲ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር የሚደራደር ቡድን መሰየሙን ሁላችንም በዜና መልክ ነው የሰማነው። ይህ ውሳኔ የፀረ ሽብር አዋጁን የጣሰ ነው። ሲቀጥልም መሰል ውሳኔዎች በመንግስት አካላት እንጂ በፓርቲ የሚወሰኑ ጉዳዮች አይደሉም። ብልጽግና ፓርቲ የሰራውን ነውር አብን ወይ ኢዜማ ቢፈጽመው ኖሮ ምን የሚከሰት ይመስላችኋል? መገመት አይከብድም። ፓርቲዎቹ በሕግ እንዲፈርሱ የመደረግ እድላቸው ይሰፋል፤ የፓርቲ አመራሮቹም በሽብር ወንጀል ተከሰው ዘብጥያ ይወርዳሉ። መሰል የሕግ ማስከበር ስራዎችም በፍትሕ ሚኒስቴርና በፀጥታ አካላት ትብብር ይፈፀማሉ። የብልጽግና ወንጀልስ? «ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡት፤ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡት» ነው ነገሩ። የፍትሕ ሚኒስትሩና የመረጃና ደሕንነት ዳይሬክተሩ አዋጁ እንዲከበር የተጣለባቸውን የሕዝብ አደራ ወደ ጎን ትተው አዋጁን ሽረው በሽብር ከተፈረጀ አካል ጋር ለመደራደር በተሰየመ ቡድን ውስጥ በአባልነት ታቅፈዋል። ከዚህ የበለጠ ኢመንግስታዊነትና ኢመደበኝነትስ ይኖር ይሆን?

በኢትዮጵያ ጉዳይ የበለጠ የሚያገባው የለም፤ እኩል ያገባናል! ተናጠላዊና የሕግ ስነስርዓቶችን ያልተከተለ ድርድር የሕግ፣ የሞራልና ማሕበራዊ ቅቡልነቶች አይኖሩትም።