Get Mystery Box with random crypto!

#እረኛዬ ምድጃ ሥር ባለ ጭስ እያሳበቡ፣ እልፍ አእላፍ እናቶች ስንት ብሶት አነቡ። ልጆች ሆነን | Christian Tadele Tsegaye

#እረኛዬ

ምድጃ ሥር ባለ ጭስ እያሳበቡ፣
እልፍ አእላፍ እናቶች ስንት ብሶት አነቡ።

ልጆች ሆነን… እረኛ ሳለን… እናናዬ የአፍ ማሟሻ፥ የናፍቆት ማስተንፈሻ ዘፈናችን ነበር። እናናዬ ዘፈን ውስጥ ምስል ከሳች እምቅ ትዝታ አለ። እናናዬ ዘፈን ውስጥ ብርቱ ፍቅር አለ።

በአናናዬ ዜማ ገራርገርነትን፣ ሩህሩህነትን ተፈጥሯዊነትን፣…ድምቀት ሰጥተን አንጎራጉረን አድገናል። ይኸን መሰሉ የልጅነት ስሜት በየጨዋታው ዓይነት መልኩን እና ዜማውን ቀያየሮ በሁላችንም የልጅነት ልብ ውስጥ ታትሞ አለ። ታዲያ ምን ሆነን ነው ስናድግ ክፉ፣ ምቀኛ፣ በጥላቻ የሰከርን የሆንነው? የልጅነት ገነታችንን ማነው ቀምቶ አሁን ወዳለንበት የመጠላላት ሲዖል ያጋዘን?

ከሰሞኑ ጋምቤላ ነበርን። ምድሩ አረንጓዴ የለበሰ፤ በባሮ የረሰረሰ፤ እግዜር የውብ ሕዝብ መኖሪያ ይሆን ዘንድ ውብ አድርጎ የሰራው የመባረክ አብነት ነው። አየሩ ሞቅ ይላል። ገነት እንዲህ ይሞቃል እንዴ ብለን አብረን የነበርን የምክርቤት አባላት ተሳስቀናል። የሄድንበትን ደቋና ወደ ማገባደድ እያለን መንገድ ላይ ሁለት ጉብሎች አየን። በግምት 12 ወይ 13 ዓመት የሚሆናት ልጅ ከጓደኛዋ ጋር ትጓዛለች። አተኩራ ተመለከተችን። ዓይኖቿ ውስጥ ተማጽኖ ነበር። በዓይኖቿ መስኮት ወደ ውስጥ ገባሁ። የተሰበረ ቅስሟ…እንክትክት ያለው ኅልሟ …ብዙ አላራመደኝም። ምልከታችን የግል ሆኖ ስለልጅቷ የምክርቤት አባላት የነበረን መረዳትና ስሜት ግን አንድና ያው ነበር። በተሰበረ ቅስሟ የሁላችንም ስሜት ተረብሿል። ወደ ሌላ ብርቱ ደቋና እየሄድን ስለነበር ልጅቷን አላነጋገርናትም። ስለሁኔታው ያወራነው ቆይተን ስለነበር ድጋሚ ሄደን ለማግኘት እድሉ አልነበረንም።

አንቺ የባሮ ዳር ጉብል ስምሽን አናውቀውም። የሆንሽውን አልነገርሽንም። እንዲሁ ግን ውብ ገጽታሽ፣ ያልነገርሽን ተማጽኖሽ፣ የመንፈስ ስብራትሽ፣ ፣…ከስጋችን ጋራ አዲስ አበባ ገብቷል። ነፍሳችን ፈገግታሽን ከሰረቀው፣ ኅልምሽን ካነካከተው፣…ከሱ ጋር ግን ለምን በሚል እዛው ባሮ ዳር እየቃተተች ነው።

መሪዎችና የእምነት አባቶች የጋራ ወገኖቻችንን የግፍ ጭፍጨፋ በጋራ አዝነን ልስ እንዳናወርድ እርም እያስበሉን ባለበት ወቅት በቴሌቪዥን መስኮት የሚተላለፍ ድራማ ትእይንት በየቤታችን አይተን የሆድ የሆዳችንን እያሰብን ጭምር እንድናለቅስ ሰበብ ስለፈጠራችሁልን የእረኛዬ ድራማ ቡድን አባላትን በሙሉ እናመሰግናለን።

ጥላቻ ገነትን ወደ ሲዖል የመቀየር አቅም አለው!