Get Mystery Box with random crypto!

ከአብን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት መልቀቄን ስለማሳወቅ፤ * የምወዳችሁ የአብን አባላትና ደጋፊ | Christian Tadele Tsegaye

ከአብን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት መልቀቄን ስለማሳወቅ፤
*
የምወዳችሁ የአብን አባላትና ደጋፊዎች ይህን እስከዛሬ ድረስ በግልጽ ባለመናገሬ እጅጉን አዝናለሁ። ይሁንና ጉዳዩን ከዚህ በላይ ማዘግየት ንቅናቄያችን የተሟላ ሁለንተናዊ ሪፎርም እንዳያደርግ እንቅፋት ስለሚፈጥር እና በለውጥ ፈላጊ ብርቱ አባላትና ደጋፊዎቻችን ዘንድ የተሰነቀውን በጎ ተስፋ ጨርሶ እንዳያጨልም ስጋት ስላደረብኝ ዛሬ የግድ ኃቁን መናገር ይኖርብኛል።

በተጨባጭ ከግንቦት 1፣ 2014 ዓ/ም ጀምሮ እንደሥራ አስፈፃሚ ተወስነው መሰራት የነበረባቸው ጉዳዮች ለውጥ ፈር በሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ምክንያት ከስነስርዓት ውጭ እየተወሰኑ በመሆኑ የእኔ በስም ብቻ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተብሎ መቀጠል ትክክል አለመሆኑን ተረድቻለሁ። የቤት ኅመማችንን በቤት ተነጋግረን እንቀርፋለን በሚል በዝምታ መቆየቴም በየደረጃው ባሉ የመዋቅራችን አባላትና አመራሮች ዘንድም ለምን ኃቁን አትነግረንም የሚል ወቀሳ አድርሶብኛል። ለተቋም ማዕከላዊነትና ወንድማማችነት እሴት በሚል በዝምታ መቆየቴ ድርጅቱን ከማዳን ይልቅ እንዲፈርስ የመተባበር ያህል በመሆኑ እያደር ስጋት ፈጥሮብኛል።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸው ሁኔታዎች ተደማምረውበት በተለይም የለውጡ ሂደት የመደናቀፍ ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠበት በመሆኑ፤ መላው የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎችም ይኸንኑ ተገንዝባችሁ፥ አብንን እንደድርጅት ለማስቀጠልና የሚጠበቅበትን ትግል በማድረግ የቆመላቸውን የፖለቲካ ግቦች ያሳካ ዘንድ፥ የሚቻላችሁን በጎ ሚና እንድትወጡም ጥሪዬን አቀርባለሁ። እንደአብንን መስራች፣ ፓርቲውን ወክሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል እንደሆነ ኃላፊነት እንደሚሰማው ግለሰብ እና እንደ አንድ አማራ ንቅናቄያችንን ወደ ቀደመ ሥፍራውና ትክክለኛው የትግል መስመር ለመመለስ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ አንዳችስ እንኳን የምቆጥበው ነገር እንደማይኖረኝም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ጋዜጣዊ መግለጫዎችንም የምንሰጥ ይሆናል።