Get Mystery Box with random crypto!

እምቡቸሬ ከባሮ ወንዝ ዳር **** እምቡቸሬ እምቡቸሬ አንጉችልኝ ከዘሬ ከሽንብራው ጎታ የተረፈውን | Christian Tadele Tsegaye

እምቡቸሬ ከባሮ ወንዝ ዳር
****
እምቡቸሬ እምቡቸሬ
አንጉችልኝ ከዘሬ

ከሽንብራው ጎታ የተረፈውን
ከጤፉ ጉሽጉሻ የተረፈውን
ከበቆሎው ጎታ የተረፈውን
መጁን ወቅረሽ
ቋቱን ጠርገሽ
ተንጎዳጉደሽ አንጉችልኝ
ጅራፍ ልግረፍ ደስ ይበለኝ

እምቡቸሬ እምቡቸሬ
እናቴ የሰጠችኝ የጤፍ ፍሬ

ያልነቀዘው ቀይ ጤፉ
የማይ…ታማው ነጭ ጤፉ
እሱን ፈጭተሽ አንጉችልኝ
ቁስሉ እንዲሽርልኝ

ጥቁር ሽንብራ
ከቂም ተራራ
ጥቁር ዳጉሳ
ከክፋት ጓሳ
ቀይ በቆሎ
ከጓሮ በቅሎ

ሁሉን ፈጭተሽ
ባንድ አንጉተሽ
አቅርቢልኝ
ይሻርልኝ

ግራ ቀኝ
ቀኝ ግራ
ማዶ ተራራ የጮኸው ጅራፍ
ፍቅርን ተክቶ ጥላቻን ያርግፍ
ቀኝ ግራ
ግራ ቀኝ
ከቤቴ ደጃፍ
ምገርፈው ጅራፍ
ጥላቻ ቂምን እንደጠል ያርገፍ

እምቡቸሬ
እምቡቸሬ
ሰላም ይወርድ ለሀገሬ

ጨለማው ተገፈፈ
ጥላቻ ተገረፈ
ቂም ረገፈ
እምቡቸሬ…

(የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝሙር 74: 14)

እንኳን ለእምቡቸሬ/ቡሄ/ ደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!