Get Mystery Box with random crypto!

#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አምላክ_ዘለዓለም_ሥላሴ_አሜን። #እንኳን_ለእመቤታችን_ | ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አምላክ_ዘለዓለም_ሥላሴ_አሜን።

#እንኳን_ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም_ጾመ_ፍልሰታ የፍቺ በዓል ና ለእመቤታችን የትንሳኤና የዕርገት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ!

በአጽናፈ ዓለም የምትኖሩ/የምትገኙ ውድ የክርስትና እምነት ተከታዮች የተዋህዶ ልጆች ክርስቲያናዊ ሰላምታችን በቅዱስ እግዚአብሔር ስም ይድረሳችሁ፡፡

#የእመቤታችን_ትንሣኤና_ዕርገት_

ነሐሴ 16 ቀን የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ያረገበት ዕለት ነው።
#እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም በዚህ ምድር የኖረችው ስልሳ_አራት ዓመት ነው፡፡ እነዚህ ዓመታት ሲተነተኑ ሦስት ዓመት በወላጆቿ ሐናና ኢያቄም ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አሥራ አምስት ዓመት ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ነው፡፡
እመቤታችን እመ አምላክ በስዕለት የተወለደች ፣ በጸጋ የተሞላች፣ ባለሟልነትን የተጎናጸፈች፣አምላክን በአጭር ቁመት ፣በጠባብ ደረት የወሰነች፣የመለኮቱ እሳትነት ስጋዋን ሳያቃጥላት አምላክ ፈጣሪዋን ጸንሳ የወለደች ፣ በግብፅ በርሃ በስደት የተንከራተተች፣ በእውነቱ የህይወትን ምግብ አዝላ ስለእኛ የተራበች ፣የተጠማች፣ ከመዓር ከስኳር የሚጥም ጡቶቿን ያጠባችው ልጇ በቀራኒዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ሲሞት መሪር እንባን ያለቀሰች፣ ለቅዱሳን ስደትን ለመባረክ ምሳሌ በመሆን የተጓዘች የተንገላታች ... ድንቅ ዘለዓለማዊ እናት ነች። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በቅዳሜ አርጋኖን ሶስቱ ያልተከፈቱ ደጆች ይልና ። ያብራራል ። አንድም በድንግልና መጽነሷን፦ ድንግልናዋን ሳይለውጠው እግዚአብሔር ወልድ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የመጸነሱ፤ በሁለተኛ ደረጃ ክርስቶስን በምትወልድበት ጊዜ የሴቶች ልማድ ሳያገኛት በጥበበ እግዚአብሔር መውለዷ፤ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ከወለደችው በኋላ ማህተመ ድንግልናዋ አልተፈታም። እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግል ናት። የስጋ ብቻ ያይደለ የሀሳብም ድንግል ናት።

አጠር ባለ አገላለጽ አምላክን ከመውለዷ በፊት፣ አምላክን በምትወልድበት ጊዜ እና አምላክን ከወለደች በኋላ ፍጹም ዘላለማዊ ድንግል መሆኗን ሊቁ ያስረዳል ። እመቤታችን ጥር 21 ቀን በ50 ዓ.ም ከዚህ አለም ድካም አርፋ ወደ ልጇ ተጠርታ ሄዳለች።

ወላድተ አምላክ ባረፈችበት ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያት ክቡር ሥጋዋን ለማሳረፍ ወደ ጌቴ ሴማኒ ሲሔዱ አይሁድ "ቀድሞ ልጇ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ተመልሶም ይህን ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ በማስተማር ሕዝባችንን ወስደውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷም እንደ ልጇ ተነሳች እያሉ በማስተማር ሊያውኩን አይደለምን? ኑ! ተሰብስበን በእሳት እናቃጥላት" ብለው ክፉ ምክር ተማከሩ፡፡

አይሁድም ከተማከሩ በኋላ ከመካከላቸውም ብርቱ ጉልበተኛ ሰው የሆነው #ታውፋንያ የተባለ ቅድስት ሥጋዋን ከሐዋርያት ነጥቆ ለማስቀረት ክቡር ሥጋዋ ያለበትን የአልጋ ሸንኮር ሲይዝ በመልአከ እግዚአብሔር እጁ ተቆርጣ ከአልጋው ላይ ተንጠልጥላ ቀረች፤ ከዚህ የጥፋቱ ሥራው ተምሮ እመቤታችንን በመለመኑ እመቤታችን የተቆረጠች እጁን መልሳለታለች፡፡

ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የተቀደሰ ሥጋዋን ጌታችን ይወደው የነበረ ተብሎ የተነገረለት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሆነውን ሁሉ ለወንድሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ነገራቸው፡፡ እነሱም የእመቤታችን ሥጋ በክብር ለማሳረፍ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ፡፡

ከሁለተኛ ሱባኤ ቆይታቸው በኋላ በአሥራ አራተኛ ቀናቸው ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ ሰጣቸው፡፡ ሐዋርያትም በዝማሬና በታላቅ ምስጋና በጌቴ ሴማኔ ቀበሯት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት› › ተብሎ ትንቢት የተናገረውን ሲተረጉሙት ‹‹ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታሳርፈው የመቅደስህ ታቦት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ›› ብለው ያመሰጥሩታል፡፡ /መዝ. 131፥8/፡፡

የእመቤታችንን ቅድስት ሥጋዋን ሐዋርያት ሲቀብሯት በሀገረ ስብከቱ ሕንድ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመናሰረገላ ተጭኖ ሲመለስ እመቤታችን ስታርግ አገኛት። ለማረጓ ምልክት ይሆን ዘንድ ለምልክት እንዲሆነው ሰበኗን (የመግነዟን ጨርቅ) ተቀብሏት ይለያያሉ፡፡ ለወንድሞቹ ለቅዱሳን ሐዋርያት ያየውን ምስጢር/የተመለከተውን ድንቅ ተዓምር/የወላድተ አምላክን ዕርገት ነገራቸው፡፡

እመቤታችን ለበረከት የሰጠችውንም ሰበን አሳያቸውና አካፈላቸው ፤ ሐዋርያት ‹ ‹ዕርገቷን እንዴት እሱ ብቻ ተመልክቶ ለምን እኛ ይቀርብናል› › ብለው በዓመቱ ነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ገቡ፡፡ ነሐሴ 16 ቀን የልባቸው መሻት ተፈጸመላቸው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቀ (ረዳት) ቄስ፣ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና ዲያቆን) አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው፡፡

በንጽህና፣ በፍጹም እምነት ፣በትኅትና የያዙት በተስፋ የጠበቁት በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ያቀረቡት ሱባኤም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገቷን ለማየት አበቃቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን መሠረት አድርጋ ከነሐሴ 1-16 ጾመ ፍልሰታ በማለት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ አድርገን እንድንጠቀምበት ሥርዐት ሠራችልን፡፡

በቅዱሳን አበው በነቢያትና በሐዋርያት በቅዱሳን ሁሉ መሠረት ላይ የታነጽን ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች በየዓመቱ ይህን ጾም በሱባኤ በማሳለፍ ከእመቤታችን ጸጋና በረከት ተሳታፊዎች እንሆናለን፤ ሆነናልም፡፡ ለቅዱሳን ሐዋርያት ትንሳኤዋን ፣ ዕርገቷን እንደገለጸችላቸው ለእኛም ምስጢርን ፣ እውቀትን ታድለን ። ትግለጽልን ። የአመት ሰው ይበለን። መልካም በዓል

ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከወላድተ አምላክ በረከት፣ረድኤት ፍቅር፣ምልጃና ጸሎት ተካፋዮች ያድርገን፡፡
አሜን!
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን
#ለወዳጅዎ_ዘመድ_ ፣_ለተዋህዶ_ልጆች #ሼር_ያድርጉ!
@mahiberekidusan
@mahiberekidusan
@mahiberekidusan