Get Mystery Box with random crypto!

#በስመ-አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን መንፈሳዊ ግጥም | ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

#በስመ-አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን

መንፈሳዊ ግጥም

#ደብረ_ታቦር

ከደብሮች ሁሉ ልቀሽ
እውነት ብርሃንን አጥልቀሽ
ተንቀሽ የነበርሽ ተራራ
አንቺ የምሥጢር ሥፍራ
የመለኮት ብርሃን በር
የሥሉስ ቅዱስ ምሥጢር
ልቆ የታየብሽ መንደር
ደብረ ታቦር!!!
ከአድማሳት ከፍ ከፍ ብሎ
የስምሽ ተረፈ ውሉ
የተዘከረው በዓለሙ
ምን ይሆን ወርቅ ሰሙ?
ምን አገኘሽ ያኔ ታቦር
እንዲያ ተከፍቶ የብርሃንሽ በር
የክብሩ ግርማ የዋጠሽ
እኮ ማን ነው የረገጠሽ?
ጌታሽ ነው አሉ ስሰማ
ከተራራሽ አናት ማማ
የብርሃን ጉንጉን ሸማ
ያጎናፀፈሽ በግርማ
ግሩም እኮ ነው!
ከተራሮች አንቺን መርጦ
ከነአባቱ ተገልጦ

ደጅሽን ሳይንቅ ማክበሩ
እንዴት እንዴት ይሆን ምሥጢሩ?
ይህንንም ደግሞ ዳዊት
ተናግሯል አሉ በትንቢት
ታቦር ወአርሞንኤም በሚል ቅኔ
በስሙ ተደሰቱ ያኔ
እያለ ዘመረ በክብር
የዚህችን ተራራ ምሥጢር
ያ ልበ አምላክ ዳዊት
የተናገረው ትንቢት
ለካ ይህ ኖሯል ግቡ
ደጅሽ በብርሃን ማበቡ
ኧረግ! አንቺስ ታድለሻል
የማይቻለውን ችለሻል
እሳተ መለኮትን ይዘሻል
ለመሆኑ እንዴት ቻልሽው ታቦር
ያን እውነተኛ ፍቅር?
ከመንበሩ የሳበው ንጉሥ
በብርሃን ሠረገላው ሲፈስ
መሠረትሽ ሳይናጋ
ባለበት ቆሞ የረጋ
ምን ይሆን ምሥጢሩ የፅናትሽ
በፊቱ ቆመሽ መታየትሽ?
ልብሱ ነጭ ሆኖ በረድ
አብም ከሰማይ ሲወርድ
ዙሪያው በክብር ደመና
ተመልቶ በብርሃን ፋና
ሙሴ ከመቃብሩ ተጠርቶ
ኤልያስ ከብሄረ ሕያዋን መጥቶ
በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው
ሲወያዩ ላስተዋለው
ምን ይመስል ይሆን ገጹ?
የብርሃን መለኮት መገለጹ
ደግሞ የሐዋርያቱ
የእነዚያ የሦስቱ
ሲጋልቡ ርደው
እንደ ቄጤማ ወርደው
ከሰሩ የተነጠፉቱ
ምንድን ይሆን ምክንያቱ?
ጴጥሮሰማ ተሽብሮ
ናላው በድንጋጤ ዞሮ
ለእያንዳንዳችሁ በጋራ
ሦስት ዳሶችን እንስራ

ብሎ በዚያች የብርሃን እልፍኝ
የዘለዓለም ደስታን ሊያገኝ
አስቦ በቅጽበት መመኘቱ
ገርሞትም አይደል ክስተቱ
የብርሃን ፀዳል ድምቀቱ?
እኮ እንደምን አይገርመው
ሙሴና ኤልያስ ቆመው

ክብሩን ሲያውጁ እያዩ
ማነው የሙሴን አምላክ ሙሴ ባዩ?
ሲል ሙሴ ባሕር ከፋዩ
የኤልያስንስ ክብር ጌታ
አውርደውት ከሰው ተርታ
ኤልያስ ባዮቹ እነማን ናቸው?
ሲል ኤልያስ ገርሟቸው

ይህን ሲሰሙ ሐዋርያቱ
በድንጋጤ ሲመቱ
ደግሞ ወርዶ አባቱ
ልጄን ስሙት በማለቱ
በፍርሃት ማዕበል ሲንገላቱ
ይህ ሁሉ ምስጢር መታየቱ
በአንቺም አይደል ታቦር
መገለጹ የሦስትነት ምስጢር
ጥንትስ ታሪክሽ ተዘክሮ
መቼ ያልቅና ተነግሮ
እንዲያው ድንቅ
እንበል እንጂ ድንቅ ድንቅ!
የብርሃንሽ ሰንደቅ
ከአድማሳት ልቆ ሲደምቅ

ክብር እንበልሽ ክብር!ክብር!
አንቺ እውነተኛ የምስጢር በር
የሥሉስ ቅዱስ ነገር
የተገለጸብሽ መንደር
ደብረ ታቦር!!!
ያበራሽ ይብራ ስሙ ይግነን
ዛሬም ለእኛ ብርሃን ይሁነን
ገኖ ያግነን በፈቃዱ
በራ ይሁንልን መንገዱ
ክብሩም ከፍ ከፍ ወደ ላይ
ከሰማየ ሰማያት በላይ
እንዲሁም በምድር በቀላይ
የአምላካችን አዶናይ
ክብርሽ ዛሬም ነገ ይነገር
መሆንሽ እውነተኛ የብርሃን በር
የሥሉስ ቅዱስ ምስጢር
የተገለጠብሽ መንደር ደብረ ታቦር!!!

ልዑል አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር በብርሃነ መለኮቱ ዘመናችንን ፣ ህይወታችንን ያብራልን። መልካም በዓል

ወስበሐት ለእግዚአብሔር።
@mahiberekidusan
@mahiberekidusan
@mahiberekidusan