Get Mystery Box with random crypto!

ርእሰ ዐውደ ዓመት ዐውደ ዓመት መነሻው ዖደ ከሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ዖደ ዞረ፤ዐውድ | ማኅበረ ቅዱሳን ( Mahibere Kidusan)

ርእሰ ዐውደ ዓመት

ዐውደ ዓመት መነሻው ዖደ ከሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ዖደ ዞረ፤ዐውድ ዙርያ፣ ማለት ነው፤ ዐውደ ዓመት የፀሐይ ዐውደ ዓመት ፫፻፷፭ ዕለት ከሩብ ይላል፡፡ (ምንጭ፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰወ ወግስ ወመዘግበ ቃላት ገጽ ፮፻፹፯)፡፡ ወበዐውዱ ለወእቱ መንበር፡፡ ይቀውሙ ዐውዶ፡፡ ዐውደ ጸሓይ፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት (ራእ.፬፡፬፤ አቡሻህር ፳፫)

ዐውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ ይባላል፡፡ ርእሰ ዐውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ መፅምቅን ያወሳናል፤ የቅዱስ ዮሐንስ ዕረፍት (ምትረተ ርእሱ) የሚታሰበው መስከረም ሁለት ቀን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ መካከል የነበረ መሸጋገሪያ ነው፡፡ መታሰቢያ በዓሉም የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ከሆነው ካለፈው ዓመት የሐዲስ ኪዳን ምሳሌ ወደሚሆነው አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ በሆነው በመስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡ቅዱስ ዮሐንስ በነቢያት መጨረሻ በሐዋርያት መጀመሪያ ተገኝቶ ዘመነ ሐዲስን እንደሰበከና ከዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ስለነበረ ያለፈውን ዘመን የምንሸጋገርበት የዘመን መለወጫ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ (ማር.፩፥፪-፭)

የዘመን ቆጠራ ከጌታችን ልደት በፊት የነበረው አገልግሎት የሰው ልጆች ሁሉ በተለይ አበው ነቢያት/ በተስፋ ይጠብቁት የነበረውን የጌታችንን መምጣት የቀረውን ጊዜ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን አጽዋማትና በዓላት ለማወቅ ነበር፡፡ ተስፋው ከተፈፀመ በኋላ ደግሞ የዘመን ቆጠራ ዋና አገልግሎቱ በዓላትና አጽዋማት በዓመቱ የሚወሉበትን ዕለት ለማወቅ ነው፡፡ እነዚህ በዓላት እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ለሰው ልጆች ያደረጋቸው ድንቅ ነገሮችና ውለታዎች የፈጸመባቸው ስቅለት፣ ትንሣኤ እና ሌሎችም በዓላት የሚታሰቡባቸው ናቸው፡፡