Get Mystery Box with random crypto!

በዚሁም መሠረት የተሰየሙት አስመራጭ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ ባወጣው የእጩ | ማኅበረ ቅዱሳን ( Mahibere Kidusan)

በዚሁም መሠረት የተሰየሙት አስመራጭ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ ባወጣው የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት መመልመያ መስፈርት መሠረት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጥቆማ ከቀረቡላቸው 75 ቆሞሳት መካከል በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በአሠረ ምንኲስናቸው፣ በቋንቋ ችሎታቸውና መንፈሳዊ አገልግሎታቸው መስፈርቱን አሟልተው የተገኙትን 18 እጩ ቆሞሳትን ከነሕይወት ታሪካቸው የተሟላ ሪፖርት ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርበዋል፡፡
 
ቋሚ ሲኖዶስም የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በቀረቡት እጩ ቆሞሳት ላይ ምርጫ እንዲደረግ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ባስተላለፈው የስብሰባ ጥሪ መሠረት ከሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረገው የ2 ቀን ስብሰባ በሁለት ዓበይት አጀንዳዎች ማለትም በእጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ችግር ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡ 

በዚሁም መሠረት፡- 1ኛ. የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በተመለከተ፡- 
 
1. ቆሞስ አባ ሣህለማርያም ቶላ ………….. ለምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት
2. ቆሞስ አባ ወ/ገብርኤል አበበ……………. ለምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት  
3. ቆሞስ አባ ጥላሁን ወርቁ………………. ለምሥራቅ ሐረርጌሀገረ ስብከት
4. ቆሞስ አባ አምደሚካኤል ኃይሌ……….. ለሆሮ ጉድሩሀገረ ስብከት     
5. ቆሞስ አባ ኃይለማርያም ጌታቸው……… ለድሬዳዋ ሀገረ ስብከት
6. ቆሞስ አባ ዘተ/ሃይማኖት ገብሬ………… ለምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት
7. ቆሞስ አባ አስጢፋኖስ ገብሬ…………… ለቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት
8. ቆሞስ አባ ክንፈገብርኤል ተ/ማርያም….. ለጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት
9. ቆሞስ አባ ስብሐት ለአብ ኃይለማርያም… ለዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት
በኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾሙ የተመረጡ ሲሆን በዓለ ሢመቱንም በተመለከተ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ 

2ኛ. በክልል ትግራይ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባትና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋና ባለማጽናናቷ፣ ጦርነቱ ቁሞ በአገር አቀፍ ደረጃ እርቀ ሰላም ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ፣ በዚሁም የተነሣ በቤተ ክርስቲያኗና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታና አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ ጠይቋል፡፡  

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም 
አዲስ አበባ   
ኢትዮጵያ