2022-09-01 07:19:09
✞✞ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት ✞✞
ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት
በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀዳሚና ተቀባይነት ያላቸው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም የምትቀበላቸውና
ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ምንጭነት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው አበይት
ጉባኤያት 3 ናቸው፡፡
እነዚህም
1- ጉባዔ ኒቅያ በ325 ዓም
2- ጉባዔ ቁስጥንጥንያ በ381 ዓም እና
3- ጉባዔ ኤፌሶን በ431 ዓም ናቸው፡፡
1) ጉባኤ ኒቅያ (በ325 ዓ.ም)
የኒቂያ ጉባኤ የተጠራው የአርዮስን ክህደት ለመቃወም ነው፡፡
የአርዮስ ክህደት መነሻ ያደረገው በምሳ. 8፡22 ያለውን ቃል ነው
ማለትም ‹‹እግዚአብሔር ዓለማትን ሳይፈጥር አስቀድሞ
ፈጠረኝ›› የሚለውን በማንሳት ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› እያለ
ማስተማር ጀመረ፡፡ በዚህ አካሄዱ ብዙዎችን ማሳሳት ጀመረ
የእስክንድርያ ሊቀጳጳስ አለ እስክንድሮስ ከክህደቱ እንዲመለስ
ብዙ ጣሩ ነገር ግን እርሱ ሊመለስ አልቻለም እንደውም ከ320
ጀምሮ ክህደቱን ማስፋፋት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ እለ
እስክንድርዮስ 100 የሚያህሉ ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ ክህደቱን
አስረዳቸው፡፡ ጉባኤውም የአርዮስን ክህደት ከመረመሩ በኋላ
አወገዙት ጉዳዩ በእስክንድርያ ብጥብጥና ሁከታን እያስከተለ
በመሄዱ ንጉሱ ቆስጠንጢኖስ የስፔንኑን ኤጲስ ቆጶስ ሆስያስን
ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ ከኤጲስ ቆጶሳት ጋር ሲወያይ ሰንብቶ
ወደ ንጉሱ ተመለሰ፡፡ ጉዳይ በሽምግልና መፍታት እንደማይቻል
ለንጉሱ አስረዳው፡፡ ከዚህ በሁዋላ ጉባኤው እንዲደረግ
ተወስኗል፡፡
ጉባኤው በአርዮስ ክህደት ላይ ተወያይቶ አርዮስና ተከታዮቹ
የወልድን የባህርይ አምላክነት በመቃወም የጠቀሳቸው ጥቅሶች
የተሳሳቱ እንደሆኑ አስረድቷል፡፡በዚህም መሠረት በምሳሌ 8÷22
የተጠቀሰው ጥቅስ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ዓለም ከመፈጠሩ
በፊት ከአብ ባህርይ መገኘቱን (መወለዱን) እንጂ እንደፍጡራን
ሁሉ ያልተፈጠረ መሆኑን አርዮስ እንዲረዳው የጉባኤው አባቶች
ብዙ ደክመዋል፡፡ ከቅዱሳት መጽሐፍትም ቃል እየጠቀሱ ቃለ
እግዚአብሔር ወልድ የባህርይ አምላክ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ወልድ የአብ የባህርይ ልጅ አንጂ ያልተፈጠረ መሆኑን ለማስረዳት
የተጠቀሱትም (ዮሐ 1÷1-14 እና 14÷30 ሮሜ 9÷15 ፤ 1ዮሐ
5÷20) እና እነዚህን የመሳሰሉት ናቸው፡፡
አርዮስ ከክህደቱ ሊመለስ ባለመቻሉ 318 ቅዱሳን አበው
በመንፈስ ቅዱስ ‹‹እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል
ተናጋሪ›› በመሆን አርዮስን አውግዘው የወልድን አምላክነት
የሚገልጽ የሃይማኖት አንቀጽ አፀደቁ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በ318
ሊቃውንት በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነውን ውሳኔ ተቀብላ
ታስተምራለች፡፡
2) የቁስጥንጥንያ ጉባኤ (381 ዓ.ም)
የቁስጥንጥንያ ጉባኤን የተሰበሰቡት በ381 ዓ.ም ነው፡፡ ጉባኤውን
የተሰበሰቡበት ምክንያቶች የመቅዶንዮስን፣ የአቡሊናርዮስንና
የአውሳብዮስን ክህደቶች በመስማት ነው፡፡
የመቅዶንዮስ ክህደትም የመንፈስ ቅዱስን ከአብና ከወልድ ጋር
በባህርይ በመልክ አንድ አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከሰረፀ
አብ እና ወልድም መንፈስ ቅዱስን ከላከና መልዕክተኛ ከሆነ
ከእርሱ ጋር ትክክል አይደለም ከእነርሱ በታች (ህፁፅ) ነው
የሚል ነበር፡፡ ይህ ትምህርቱም በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት
መዛመት ስለጀመረ አንድ መቶ ሃምሳ (150) ኤጲስቆጶሳት
በቁስጥንጥንያ በ301 ዓ.ም ተሰብስበው ዐቢይ ጉባኤ አደረጉ፡፡
በዚህ ጉባኤ ከብሉያትና ከሐዲሳት እየጠቀሱ መንፈስ ቅዱስ
ከአብ ቢሰርፅም ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ በመለኮት አንድ
መሆኑን ከእነርሱ ጋር ትክክል መሆኑን (መዝ. 33፡6፤ ኢሳ. 6፡3፤
የሐዋ. 28፡28) በመጥቀስ ትምህርቱን አውግዘዋል፡፡
በኒቂያ 318 ቅዱሳን አበው የወሰኑትንም አንቀጸ ሃይማኖት
በማጠናከር የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት በሚገባ ገልጸው
‹‹ከአብ የሰረፀ ጌታ ሕይወት ሰጭ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ
እናምናለን ከአብ እና ከወልድ ጋር እንሰግድለታለን እርሱም
በነቢያት አድሮ የተናገረው ነው›› ብለው በኒቂያ የሃይማኖት ውሳኔ
ላይ ጨምረው ወሰኑ፡፡
3) የኤፌሶን ጉባኤ (431 ዓ.ም)
- ጉባኤ ኤፌሶን በ431ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ በ200 ሊቃውንት
የተካሄደ ነው፡፡ የስብሰባው መሪ ቄርሎስ ነበር፡፡
- የስብሰባው ዋና ምክንያት የንስጥሮስ ክህደት ነው፡፡
- ንስጥሮስ የተማረው በአንጾክያ ሲሆን ክህደቱም ለክርስቶስ
ሁለት ባህሪያት አሉ፡፡ አምላክም ሰው የሆነው በንጽረት ነው፡፡
ንጽረት ማለትም እመቤታችን የወለደችው ሰውን ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ እርሱአም ወላዲተ አምላክ አትባልም የሚል ነው፡፡
- ንስጥሮስን ተከራክሮ የረታውና መልስ ያሳጣው
እስክንድርያዊው ሊቀጳጳስ ቄርሎስ ነው፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ
"የእግዚአብሔር ልጅ በማርያም አደረ፡፡ በመከራም ጊዜ ተለየው"
የሚሉ ንስጥሮስንና ወገኖቹን የተጠቀሰውን የማርያም ልጅ ብቻ
ከሆነ ጥያቄ በክህደትና በድፍረት የተከፈተ አፋቸውን አስይዞ
ይመልሳቸው እንደነበር የቤተክርስቲያን ፀሐፊዎች ዘግበውታል፡፡
የአባቶቻችን በረከት በሁላችን ላይ ይደር፡፡
ምንጭ፡- የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በከፊል የተወሰደ
66 viewsⓋⓐⓣⓛⓚⓐⓝⓐ, 04:19