Get Mystery Box with random crypto!

#መተሐራ በትላንትናው ዕለት በ #መተሐራ_ከተማ በደረሰ ጥቃት 6 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ 8 ሰ | ልዩ መረጃ ®

#መተሐራ

በትላንትናው ዕለት በ #መተሐራ_ከተማ በደረሰ ጥቃት 6 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ 8 ሰዎች ተገደሉ።

በመተሐራ እና አካባቢው ያሉ የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት አሁንም በታጣቂዎች እየደረሰ ያለው ጥቃት መቀጠሉን ገልጸዋል።

በትላንትናው ዕለትም ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 6 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 8 ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰዋል።

ጥቃቱ ትላንት ሐሙስ መጋቢት 07 ቀን 2015 ምሽት 3:00 አካባቢ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ህይወታቸው ካለፉ ሰዎች በተጨማሪ በ4 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነው የገለጹልን።

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከልም ወደ አዳማ ሪፈር የተጻፈላቸው መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት።

አንድ የቤተሰባችን አባል ፦ " ሌሊት ላይ መጥተው ሰው ገድለው ነው የሚሄዱት፤ ከ6 ወር በፊት 15 ሰዎች ገድለዋል፤ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ እንዲሁ 4 ሰዎች ተገድለው ነበር። ትላንትና ደግሞ የጎዳና ልጆችን ጨምሮ 8 ሰዎችን ገድለዋል ፤ ማን እንደገደላቸው አይታወቅም፤ ያው ሁል ጊዜ ሸኔ ነው የሚባለው እንደዛ እየተባለ ነው እስካሁን መለየት አልቻልንም። ...መከላከያ በተደጋሚ ይመጣል፤ እነርሱ ሲመጡ እነዚ ይሸሻሉ ከዚያ ደግሞ ትንሽ መከላከያ ራቅ ሲልላቸው መጥተው ሰዎች ይገላሉ። " ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

አክለውም ፤  " በከተማችን ጥቃቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸም ሲሆን የዚህኛው ዙር ጥቃት እጅግ ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ በጎዳና ላይ የነበሩ ልጆች ላይ የተፈጸመ በመሆኑ በጣም አሳዛኝ ነው። ይህ ምንም ዓላማ የሌለውና ህብረተሰቡን ለማሸበር የተደረገ ነው " ሲሉ ገልፀዋል።

ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት መብራት እንዲሁም ኔትዎርክ ጠፍቶ እንደነበር የገለጹልን የመተሀራ ቤተሰቦች "ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ፊሽካ ነፍተው ከከተማው ሸሹ፤ ይህ ከዚህ በፊት በነበሩት ጥቃቶችም በተደጋጋሚ የተደረገ ነው። " ሲሉ መረጃቸውን አድርሰዋል።

ስለደረሰው ጥቃት እንዲሁም ጥቃቱን ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ አካላት ስለወሰዱት እርምጃ ከከተማው ከአስተዳደር አካላት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።