Get Mystery Box with random crypto!

ኢዜማ ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት “መልሶ ለማጤን” የሚያስችል ጥናት ሊያካሄድ ነው ተባለ! | ልዩ መረጃ ®

ኢዜማ ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት “መልሶ ለማጤን” የሚያስችል ጥናት ሊያካሄድ ነው ተባለ!

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት “መልሶ ለማጤን” የሚያስችል ጥናት የሚያደርግ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን የፓርቲው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገለጹ። የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው፤ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የፓርቲውን የአምስት ዓመት ጉዞ ትንተና የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የፓርቲው ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ግብረ ኃይሉን ያቋቋመው፤ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2፤ 2015 ባካሄደው ስብሰባ መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ተናግረዋል። ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዚሁ ስብሰባው፤ የፓርቲውን የስድስት ወራት አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን እና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርጓል።

በወይይቱ ላይ የመሪው ክንፍ ሪፖርት ማቅረቡን የተናገሩት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ፤ ፓርቲው ከመንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ላይ ውይይት እንደተደረገበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን ስንገመግም አንድ አብረን ያየነው አጀንዳ [እንጂ]፤ ለብቻው የቀረበ አጀንዳ አይደለም” ሲሉም ጉዳዩ ውይይት የተደረገበትን አውድ አስረድተዋል።

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ግን ፓርቲው “ከመንግስት ጋር ያለውን አብሮ የመስራት ግንኙነት፤ እንደገና ማጤን እንደሚያስፈልገው” ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል። ኢዜማ ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙት ለመፈተሽ የወሰነው፤ “መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች የሚሰጣቸው ምላሾች ችግሮችን የሚያባብሱ እና ሌሎች አዳዲስ ችግሮችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ነው” ሲሉ የፓርቲው ምንጮች ምክንያቱን አብራርተዋል። 

ይህንንም በተመለከተ ጥናት የሚያደርግ ግብረ ኃይል መቋቋሙን እና የሁለት ሳምንት ጊዜ እንደተሰጠው እነዚሁ ምንጮች አስረድተዋል። ከግብረ ኃይሉ ግምገማ በኋላ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፤ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ እንደሚችልም ጠቁመዋል። በኢዜማ መተዳዳሪያ ደንብ መሰረት፤ በየሶስት ዓመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው።  የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ፤ አስቸኳይ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን እንዳለው መተዳደሪያ ደንቡ ይደነግጋል።

ኢዜማ ከመንግስት ጋር ለመስራት ሲወስን “በትብብር ለውጥ ማምጣት የሚቻልባቸው ጉዳዮች አሉ” ከሚል ትንተና መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ የብሄር መጓተቶች” እንዲሁም ከሰሞኑ ከአድዋ ክብረ በዓል ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ክስተቶች “ኢዜማ ከመንግስት ጋር መስራቱ ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል” የሚሉት ዶ/ር ሙሉዓለም፤ እንዲያም ቢሆን ግን ጉዳዩ የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው “ዋነኛ አጀንዳ አልነበረም” ሲሉ አስተባብለዋል።

Via Ethiopia Insider