Get Mystery Box with random crypto!

#EOTC የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋ | ልዩ መረጃ ®

#EOTC

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አባቶች ጋር በወቅታዊ የቤተክርስትያን ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

በዚህም ውይይት ወቅት ችግሮችን ለመፍታት ቃል የገቡ ቢሆንም አሁንም ችግሮች አልተፈቱም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያቋቋመችው የሕግ ኮሚቴ አባል የሆኑት የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አያሌው ቢታኔ ለአዲስ ማለዳ የሰጡት ቃል ፦

" ፕሬዝዳንቱ በቤተክርስያን ጉዳይ የታሰሩ ሰዎች እስከ ዛሬ ማክሰኞ ድረስ ይፈታሉ ብለው ቃል የገቡ ቢሆንም፣ ሽንገላ የሚመስል ነገር እየተከናወነ ነው።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሕግን የማስፈጸም ግዴታ እያለባቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው ምክንያት አሁንም በርካታ የሕግ ጥሰቶችና የንብረት ውድመቶች እየደረሱ ነው።

ትናንት ሰኞ በፍርድ ቤት እግድ የተጣለባቸውና ከቤተክርስትያኗ ቀኖና ውጭ የተሾሙ ግለሰቦች በአሰላ የአቡነ ያሬድ መንበረ ጵጵስናን ሰብረው የገቡ ሲሆን፣ ይህም በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ድጋፍ የሚደረግ ሕገ-ወጥ ድርጊት ነው።

ሻሸመኔና አርሲ ነገሌን ጨምሮ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች አሁንም በርካታ ካህናትና ምዕመናን ያለምንም ጥፋት ታስረው ይገኛሉ።

ከዚህ በፊትም በመንግሥት በሁለት ቀን ውስጥ ይፈታሉ ተብለው የነበሩ ታሳሪዎች ሳይፈቱ በርካታ ቀናት ተቆጥረዋል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ራሱ ለገባው ቃል ተገዢ እየሆነ አይደለም። በዚህም ምክንያት ካህናትና ምዕመናን ለበርካታ ችግሮች ተጋልጠዋል ቤተክርስትያኗም ጉዳት እየደረሰባት ይገኛል።

ቤተክርሰትያኗ ከመንግስት ጋር የደረሰችው ስምምነት በመንግሥት በኩል  ሊደረግ ታስቦ የነበረውን ሰልፍ የማስቀረት ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም።

አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ እየከፋ ነው እየሄደ ያለው።

ምዕመናኑ ምንም እንኳን በሚፈጸሙ ድርጊቶች ያዘኑ ቢሆንም የቤተክርስትያን አባቶችን ትዕዛዝ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

መንግስት የገባውን ቃል አልመፈጸሙ፣ በሕግ እንዲያስፈጽም የተሰጠውን ኃላፊነት አለመወጣቱና የያዘው አካሄድ ሕዝብና አገርን ዋጋ የሚያስከፍል ነው።

ለዚህም እስከ ዛሬ ማክሰኞ ድረስ ሁሉንም ጉዳዮችና የሕግ ጥሰቶች ለማስተካከል በኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተገባው ቃል እንዲፈጸም እንጠይቃለን።

የቤተክርስትያን ጉዳይ ወደ ከፋ ነገር ሳያመራ መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል። "

በሌላ በኩል ፤ በአዋሽ ሰባት ከታሰሩ ወጣቶች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት መለቀቃቸው የተሰማ ሲሆን ወጣቶቹ ብጹአን አባቶች በቦታው ሊያደርጉት የታሰበው ጉብኝት መሰማቱን ተከትሎ መፈታታቸው ተነግሯል፡፡

ይሁንና አሁንም ድረስ በቦታው ታስረው የሚገኙ ወጣቶች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን፣ ከሰላሳ የማይበልጡት ታሳሪዎች እንዲፈቱ ጊዜያዊ የሕግ ኮሚቴው እየሰራ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

(አዲስ ማለዳ ጋዜጣ)