Get Mystery Box with random crypto!

ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ትላንት ምሽት የመንግሥት | ልዩ መረጃ ®

ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ትላንት ምሽት የመንግሥት ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል " ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ " ን አስመልክቶ የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ መግለጫ እንደማይቀበል አሳውቋል።

" መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን በጽኑ እንድናምን አድርጎናል " ብሏል።

ቅዱስ ሲኖዶስ መንግስት ከአጉል እልከኝነቱ ወጥቶ ፦

- ከሕገ ወጦቹ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ፪/ሁለት/ ቀናት ውስጥ እንዲያቆም እና ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር

- በኃይል የወረራቸውን መንበረ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቆ ለቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር እንዲያስረክብ፣

- ያለአግባብ ያሠራቸውን ካህናት እና ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ፣

- ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለፈፀመው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤

- በካህናት እና ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲክስ እና የወደሙ ንብረቶቿን እንዲጠግን በጥብቅ ጠይቋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ መንግሥት #በዚሁ_አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መብቷን ለማስከበር እስከአሁን ድረስ ፍጹም ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት 5/2015 ዓ/ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት በራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን አሳውቋል።

መንግሥት ድርሻው ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ " ዛሬም ቢሆን መንግሥት ቆም ብሎ በማሰብ ከእኛ ከአባቶች ጋር ሃይማኖታዊ ፣ ቀኖናዊ እና መንፈሳዊ የአስተዳደር ሥርዓታችንን ባልጣሰ መልኩ ለመነጋገር እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ካደረገ በውይይት ለመፍታት መንፈሳዊ በራችን ክፍት መሆኑን እናሳውቃለን " ብሏል።

ከዚህ ውጭ ግን በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ ችግር እየተባለ የሚነገረው ፖለቲካዊ ጨዋታ የመንግሥት እንጂ በሀገሪቱ ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ ግለሰቦች ጋር ማነጻጸር ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ሞራላዊ የሕግ መሠረት የለውም ሲል አስገንዝቧል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በህገመንግስቱ የተደነገገ መሰረታዊ መብት መሆኑን ገልጾ ቤተክርስቲያን የጠራችውን ሰላማዊ እና ሕጋዊ የሆነ የመብት ጥያቄ የማፈን ሂደትን በጥብቅ እንቃወማለን ብሏል። 

@leyumerga