Get Mystery Box with random crypto!

ከአላማጣ በተነሱ መንገደኞች ላይ በመተሀራ በተፈፀመ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ ከሰሜን | LEYU NEWS

ከአላማጣ በተነሱ መንገደኞች ላይ በመተሀራ በተፈፀመ ጥቃት የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

ከሰሜን ኢትዮጵያ አላማጣ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ ነበረ የተባለ፣ የኛ ባስ በተሰኘው የህዝብ ማመላለሻ ላይ ባለፈው ሐሙስ ሚያዚያ 19/2015 ምሽት 12፡30 አካባቢ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ሹፌሩ እና ረዳቱ ወዲያውኑ ህይወታቸው ማለፉን በቦታው የነበሩ ተሳፋሪዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከአምስት ያላነሱ ተጓዦች ቁስለኛ ሆነው አዳማ ከተማ ለሕክምና መወሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከተሳፋሪዎች ጋር አብረው ለእረፍት ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች አክለዋል።

ጥቃቱ አድራሾቹ የተኩስ እሩምታ ከፍተው ጉዳት ያደረሱትም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በመተሀራ እና በወለንጭቲ ከተማ መሀል ላይ ነው ተብሏል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ቁጥራቸው ከአምስት የማይበልጡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ቦታው መድረሳቸውን የገለጹት የዓይን እማኞች፤ በየኛ ባስ ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ በሚኒ ባስ ይጓዙ የነበሩ ሰዎችን አግተው ሲወስዱ ተመልክተናል ብለዋል፡፡

ጥቃት አድራሾች የተወሰኑት መደበኛ ሌሎች ደግሞ ወታደራዊ ልብስ የለበሱ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ መንገደኞች እነዚህ ኃይሎች የሸኔ ታጣቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምተዋል።

ተሳፋሪዎች ከአላማጣ በቆቦ መገንጠያ አድርገው በአፋር በርሃ በኩል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ እንደነበር ጠቅሰው፤ "የሰው ህይወት እንዲህ ተራ ሲሆን እና በሚዲያዎችም ሆነ በመንግስት ምንም ሳይባል መቅረቱ ያሳዝናል።" ሲሉ ተደምጠዋል።

በሳሙኤል ታዴ

@Leyu_News
@Leyu_News