Get Mystery Box with random crypto!

መ ሠ ረ ተ ግ እ ዝ የግእዝ ቋንቋ ታሪክና አመጣጥ ክፍል ፩(1) ቋንቋ ማለት መ | ግእዝ ሚዲያ

መ ሠ ረ ተ ግ እ ዝ


የግእዝ ቋንቋ ታሪክና አመጣጥ
ክፍል ፩(1)

ቋንቋ ማለት መግባቢያ ማለት ነው ፡፡ የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ ከአንዳንድ ቀደምት የታሪክ ጸሓፊዎችና የግእዝ ቋንቋ መጻሕፍትን ጽፈው ካስረከቡን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የቋንቋው ባለቤቶች እንደምንረዳው፦ የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ በኢትዮጵያ መነሻ ሊሆነን የሚችለው ክርስቶስ ከመወለዱ ከ800 ዓመት ጀምሮ ነገደ ሴም (የሴም ዘሮች/ወገኖች) ቋንቋቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሴማዊ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ቋንቋ ሆነ፡፡ ነገደ ሴም ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ቋንቋቸውን በመግባቢያነት አሳድገው፣ ሥነ ጽሑፋቸውን አስፋፍተው በባቢሎን ፣ በአካድና በአሶር ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለሁት ተከፍለው ግማሾቹ ሴማውያን ሰሜንና ምስራቅ እስያን፣ ግማሾቹ ሴማውያን ደግሞ ደቡብ እስያን ይዘው ይኖሩ ነበር፡፡

የሰሜን እስያ ሴማውያን ቋንቋ (የአካድ ቋንቋ)፦ አማራይክ፣ ዕብራይስጥን እና ፊንቄን ሲያስገኝ የደቡብ እስያ ሴማውያን ቋንቋም (አካድ ቋንቋ)፦ ሳባን ግእዝንና የተለያዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በመግባቢያነት የምንጠቀምባቸውን ሴማውያን ቋንቋዎች አስግኝቷል፡፡ በደቡብ እስያ ይኖሩ የነበሩ ነገደ ሴም በተለያየ ምክንያት እየፈለሱ ወደ ደቡብ ዐረብ ወደ የመንና ወደ አካባቢዋ መጥተዋል ከዝያም ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአክሱምና በአካባቢዋ ሰፍረው ይዘዋቸው ከመጡት ቋንቋዎቻቸው መካከል በታሪክ ጎልተው የሚታወቁና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓትም በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ቋንቋዎች የሳባ እና የግእዝ ቋንቋዎች ናቸው፡፡


ነገደ ሴም(ሴማውያን) ቋንቋዎቻቸውን /ሳባና ግእዝን/ ከነገደ ካም ቋንቋ ጋር አስማምተው በመያዝ ሁሉንም ቋንቋዎች ሲናገሩዋቸው ኖረው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሳባና ግእዝ እየተለመዱና እየተስፋፉ እየዳበሩም ከመሄዳቸው የተነሣ የነገደ ካምን ቋንቋ እየዋጡት መጥተው ሁለቱ ሳባ እና ግእዝ ቋንቋዎች ብቻ ሀገራዊ ቋንቋዎች ይሆኑ ጀመር እየቆዩ ግን ሁለቱ (ሳባና ግእዝ) በጣም ተመሳሳይና ተቀራራቢ በመሆናቸው እንደ አንድ ቋንቋ ሆነው ይነገሩ ጀመር፡፡ ይኸም ጽሑፉ (ፊደሉ) በሳባ እንዲጻፍ እና መነጋገሪያ ቋንቋውን ደግሞ በግእዝ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ ነገደ ሴም በሳባ ቋንቋቸው ፥ሳባውያን፥ በግእዝ ቋንቋቸው ደግሞ ፥አግአዝያን፥ ተብለው የሚጠሩት ከዚህ መነሻነት ነበር፡፡

ለዚህም መረጃ የሚሆኑን ሳባና ግእዝ ቋንቋዎች ተጽፈውባቸው የሚገኙት ጥንታውያን የኢትዮጵያ ቅርሶች እንደ የአክሱምና የላሊበላ ሐውልቶች በየሐ እና በአዱልስ ወዘተ….. የተለያዩ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችና ቅርጻ ቅርጾች እስከ አሁን ቆመው የሚገኙ የዚህ ቋሚና ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የሳባና የግእዝ ቋንቋዎች በዚህ ሁኔታ እስከ 324 ዓ.ም. አካባቢ ድረስ አብረው ሲነገሩ ቆይተዋል በኋላ ግን የሳባ ቋንቋ እየተዳከመና በግእዝ ቋንቋ እየተዋጠ ይሄድ ጀመር እንደ ምንም እየተንገዳገደ እስከ 350 ዓ.ም. ቆይቶ ከዚህ በኋላ ከሥነ – ጽሑፍ ከመነጋገሪያነትም ፈጽሞ ቀረ የግእዝ ቋንቋ ግን ከ324 ዓ.ም ጀምሮ ብቸኛ ሀገራዊ ቋንቋ በመሆን እስከ 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም የአማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል እንደ ነበር የታሪክ ጸሐፊዎች በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡


ዮም ፈጸምነ ዘይእዜ ትምህርት ሠናይ ሶቤ ይኲን ለኲልኲሙ ፡፡
ይቀጥላል...

#መጀመሪያ #ግእዝ_ታሪክ